ሸሪክ ከደንበኞቹ በአደራ መልክ የሰበሰበውን ከ16 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ
ዳሸን ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ሸሪክ ከደንበኞቹ በአደራ መልክ የሰበሰበውን 16.9 ሚሊየን ብር ለግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ አደረገ።
ሸሪክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎቶ ስምንተኛ ዓመት የምስረታ በዓሉንም በዛሬው እለት አክብሯል።
የባንኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ ተወካይና በዳሸን ባንክ ቺፍ ባኪንግ ኦፕሬሽን ኦፊሰር አቶ ጥበቡ ሰለሞን ሸሪክ በ8 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ እድገት አሳይቷል ብለዋል። ብዙ ደንበኞችን ደርሷል፣ ለህብረተሰብ ዋጋ መፍጠር ችሏል ሲሉ ተናግረዋል።
30ኛ ዓመቱን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው ዳሸን ኤክስፖ የማጠናቀቂያ መርሐ-ግብር በተከናወነበት በዛሬው ዕለት፤ የዳሸን ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ሸሪክ የ8 ዓመት የስኬት ጉዞን አስመልክቶ ማብራሪያ ተሰጥቷል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት በዳሸን ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ቺፍ ኦፊሰር አቶ አምዱ ሰማን ሸሪክ አሁን ላይ ለደረሰበት ስኬት የክቡራን ደንበኞቹ ሚና ላቅ ያለ መሆኑን ገልጸዋል።
ዳሸን ባንክ ጠንካራ የሸሪዓ አማካሪ ኮሚቴ በማቋቋም የማህበረሰቡን ዕሴቶች ያከበሩና ሸሪዓውን የጠበቁ አገልግሎቶች መስጠቱን አጠናክሮ እንደቀጠለም አቶ አምዱ አስረድተዋል።
የዳሸን ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ሸሪክ ከሚሰጣቸው ዘመናዊና አካታች የባንክ አገልግሎቶች ባሻገር ማህበራዊ ሐላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለት ለግብረ-ሰናይ ድርጅቶች የተሰጠው የገንዘብ ድጋፍ የዚሁ ተግባር አንድ አካል መሆኑን የጠቆሙት አቶ አምዱ፤ ሸሪክ በዚህ ስምንት ዓመት ውስጥ ከ1.5 ሚሊየን በላይ ደንበኞችን ማፍራት እንደቻለ እንዲሁም ከ25 ቢሊየን ብር በላይ ተቀማጭ ማድረስ ችሏል ብለዋል።
የዳሸን ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ሸሪክ ከ17 ቢሊየን ብር በላይ የተለያዩ ዘርፎችን ፋይናንስ ማድረግ እንደቻለም አስረድተዋል፡፡
ዳሸን ባንክ እ.ኤ.አ በ2023 በባህሬን ማናማ በተካሄደው 9ኛው የኢስላሚክ ሪቴል ባንክ ሽልማት ላይ በኢትዮጵያ ጠንካራው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥ ባንክ በሚል ተቀማጭነቱን ሎንዶን ባደረገው ካምብሪጅ ኢንስቲትዩት ኦፍ ኢስላሚክ ፋይናንስ ኤንድ ኢኮኖሚክስ ሽልማት መቀበሉንም አስታውሰዋል፡፡
ዳሸን ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ሸሪክ አሁን ላይ ከ90 በላይ በሆኑ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነጻ የሆኑ ቅርንጫፎችን እና በሁሉም የዳሸን ባንክ ቅርንጫፎች በመስኮት በኩል አገልግሎቱ እየተሰጠ ይገኛል፡፡
ዳሸን ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት በአለም አቀፍ ደረጃ የእስላማዊ ፋይናንስ ተቋማትን የሂሳብ፣ ኦዲት እና ሸሪዓህ መስፈርቶችን የሚያወጣው ተቋም (AAOIFI) ቋሚ አባል የሆነ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የፋይናንስ ተቋም መሆኑ ይታወቃል፡፡
