በዳሸን ባንክ የኢኖቬሽን ወር በይፋ ተጀመረ

በዳሸን ባንክ በየአመቱ የተለያዩ ከፈጠራ ጋር የተያያዙ መርሃ ግብሮች የሚከናወኑበት የኢኖቬሽን ወር ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
በባንኩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ዛሬ የኢኖቬሽን ወር ሲጀመር ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ አስፋው ዓለሙ የባንኩ ሰራተኞች ይህ ወር ለፈጠራ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳዩበት መሆኑን አመልክተው ፈጠራ በጊዜ የታጠረ አለመሆኑንና ሁሌም ተግባራዊ መደረግ ያለበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የባንኩን አጠቃላይ አሰራሮች በተለይም የደንበኞችን አገልግሎት ይበልጥ ለማዘመን የሚያስችሉ የፈጠራ ስራዎችን በውስጥ የሰው ሃይል እንዲተገበሩ በማድረግ ለወደፊት በኢንዱስትሪው ይበልጥ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚቻል አቶ አስፋው አስገንዝበዋል፡፡
ሁሉም የባንኩ ሰራተኞች በተለይም የወደፊቱ የባንኩ ተረካቢ የሆኑ ወጣቶች ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ያሏቸውን የፈጠራ ሃሳቦች እንዲያቀርቡ ዋና ስራ አስፈፃሚው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በጉባኤው ላይ የባንኩ የተለያዩ መምሪያዎች የስራ ሃላፊዎች የተሳተፉበት የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን በፈጠራ ምንነትና በደንበኞች አገልግሎት እንዲሁም ሌሎች የባንክ አገልግሎቶችን ለማዘመን በሚኖረው አስተዋፅኦ ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በፈጠራ ወር እ.ኤ.አ እስከ ጥር 15 ቀን 2026 ድረስ የተለያዩ የፈጠራ ሃሳቦች በባንኩ ሰራተኞች ቀርበው አሸናፊዎቹ ሽልማት ይበረከትላቸዋል፡፡
\

፡