Select Page

በዳሸን ኤክስፖ ላይ የደንበኞች አገልግሎት ባህልን አስመልክቶ ውይይት ተደረገ

ዳሸን ባንክ ባዘጋጀው ዳሸን ኤክስፓ ላይ በዛሬው ዕለት የደንበኞች አገልግሎት ባህልን አስመልክቶ ውይይት ተደርጓል።

ዕለቱን አስመልክቶ ንግግር ያደረጉት በዳሸን ባንክ ቺፍ ኤክስፒሪያንስ ኦፊሰር እየሩሳሌም ዋጋው ዳሸን ባንክ የደንበኞቹን እርካታ ለማሳደግ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ባንኩ የደንበኞቹን ተሞክሮ ለማሻሻል ባከናወናቸው ተግባራት የደንበኞች እርካታ መጠን ማደጉን ያብራሩት እየሩስ፤ ባንኩ የደንበኞችን ፍላጎት በቅርበት ለመረዳት እና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችለውን የደንበኞች ግንኙነት አስተዳደር ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ለማድረግ የፕሮጀክት ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።

በቅርንጫፎች የሚሰጠውን አገልግሎት ይበልጥ ቀልጣፋ ለማድረግ እና ከወረቀት ንክኪ ነፃ ወደሆነ የዲጂታል አሰራር ለመሸጋገር ሰፊ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

ደንበኞች ቅሬታቸውንና ጥያቄዎቻቸውን በ24 ሰዓት ውስጥ ምላሽ የሚያገኙበት የ6333 የጥሪ ማዕከል ተጠናክሮ መቀጠሉ ተመልክቷል።

ከኤክስፖው ጎን ለጎንም የባንኩ ሠራተኞች እና ደንበኞች የተሳተፉበት የደም ልገሳ መርሃ-ግብር የተከናወነ ሲሆን፣ ይህም ባንኩ ለማኅበራዊ አገልግሎት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ተብሏል።

​ዳሽን ባንክ የአገልግሎት ባህሉን በማዘመን፣ ደንበኞች በክብርና በቅልጥፍና አገልግሎት እንዲያገኙ በሰው ኃይል ስልጠና እና በቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራቱን እንደሚቀጥልም ተገልጿል።

በትላንትናው ዕለት በድምቀት የተከፈተው ዳሸን ኤክስፖ እስከ ቀጣዩ ቅዳሜ ሚያዚያ 24 ቀን 2018 ዓ.ም በተለያዩ መርሐ-ግብሮች ይቀጥላል።

Facebook
Twitter
YouTube
LinkedIn
Instagram
Telegram