ኦሮሚያ ሕብረት ስራ ባንክ ለዳሸን ባንክ 30ኛ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ
ኦሮሚያ ሕብረት ስራ ባንክ ዳሸን ባንክ የተመሰረተበትን 30ኛ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በባንኩ ዋና መስሪያ ቤት በመገኘት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
የኦሮሚያ ሕብረት ስራ ባንክ ቺፍ ፋናንሻል ኦፊሰር አቶ ሙሉነህ አቦዬ ዳሸን ባንክ በብዙ ነገሮች ቀዳሚ ባንክ መሆኑን ገልጸው ባንኩ በተለይም በቴክኖሎጂ መስክ አርዓያ የሚሆኑ ስራዎችን እንዳበረከተ አብራርተዋል፡፡
ዳሸን ባንክና ኦሮሚያ ሕብረት ስራ ባንክ ላላቸው ጥሩ የሚባል ትብብር ክብርና አድናቆት አለን ያሉት አቶ ሙሉነህ ይህ ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል፡፡
ዳሸን ባንክ ለባንክ ኢንዱስትሪ እና ለሐገር ኢኮኖሚ የራሱን ድርሻ እያበረከተ እንደሆነ ያነሱት አቶ ሙሉነህ ባንኩ በቀጣይም ውጤታማነቱ እንዲቀጥል መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
በኦሮሚያ ሕብረት ስራ ባንክ ማርኬቲንግ ኤንድ ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ቶሌራ ሹና በበኩላቸው እንኳን ለ30ኛ ዓመታችሁ አደረሳችሁ ያሉ ሲሆን፣ዳሸን ባንክ በባንክ ኢንዱስትሪው ላይ ያለው አዎንታዊ ተፅዕኖ ከፍ ያለ እንደመሆኑ በቀጣይም ታላላቅ ስኬቶችን እንደሚያስመዘግብ እርግጠኛ ነን ብለዋል፡፡
የዳሸን ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ተወካይና የባንኩ ቺፍ ባንኪንግ ኦፕሬሽን ኦፊሰር አቶ ጥበቡ ሰለሞን በበኩላቸው ኦሮሚያ ሕብረት ስራ ባንክ መልካም ምኞቱን ለመግለጽ በዳሸን ባንክ ዋና መስሪያ ቤት በመገኘቱ አመስግነው፣ ዳሸን ባንክ በበርካታ ዘርፎች ፈር ቀዳጅ የሆኑ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
የኦሮሚያ ሕብረት ስራ ባንክ በተለይም አርሶ አደሩን እና ህብረት ስራ ማሕበራትን ያካተቱ የባንክ አሰራሮችን በመዘርጋት አበረታች ስራዎችን እየሰራ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ይህ አካታች የባንክ አገልግሎት ለሌሎች ባንኮችም ምሣሌ የሚሆን ነው ያሉት አቶ ጥበቡ፤ ስራው እንደ ሐገር የሚኖረው አበርክቶ ከፍተኛ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ሁለቱ ባንኮች በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ትብብር እናስቀጥላለን ያሉት አቶ ጥበቡ ቀጣዩ ጊዜ ለሁላችንም የተሣካ እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል፡፡
