ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዳሸን ባንክ ተከበረ
ዳሸን ባንክ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን በሴቶች ብቻ በሚመራው ቦሌ ኖክ ቅርንጫፍ አክብሯል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ ተገኝተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የባንኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ ተወካይ አቶ ጥበቡ ሰለሞን፤ ዳሸን ባንክ ባለፋት 30 ዓመታት የስኬት ጉዞው የሴቶችን አቅም ለማሳደግ ያደረገው ጥረት ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ባንኩ ሴቶችን ወደ አመራርነት ደረጃ ለማምጣት እየሰራ ይገኛል ያሉት አቶ ጥበቡ ሴቶች እንደ ሀገር ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ባንኩ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም አመላክተዋል።
ዳሸን ባንክ የፋይናንስ አካታችነትን በማረጋገጥ የሴቶች ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየሰራ እንደሆነም ተናግረዋል።
የሴቶች አቅም ሲያድግ ሌሎችን የማበረታታት አቅም ስለሚኖረው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልጸዋል።
በዳሸን ባንክ ቺፍ ኤክሲፒሪያንስ ኦፊሰር እየሩሳሌም ዋጋው ባንኩ ሴቶችን በፋይናንስ ዘርፍ ተሳታፊ ለማድረግ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ከመደበኛው የባንክ አገልግሎት በተጨማሪ በወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ ሴቶችን በፋይናንስ ለማካተት አዳዲስ አገልግሎቶች የተዘረጉ በመሆናቸው ደንበኞች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።
ዳሸን ባንክ 30 ዓመት የቆዩት እና በባንኩ የሴልስ ሰፓርት ከፍተኛ ስራ አስኪያጅ የሆኑት ወ/ሮ አጀብ ወርቅ አሊ በባንኩ ቆይታቸው ያገኙትን ልምድ አካፍለዋል። ባንኩ ሴቶችን ለማብቃት ከተለያዩ ተቋማት ጋር እያከናወናቸው ባሉ መርሃ-ግብሮች ተሳታፊ በመሆን ሴቶች ራሳቸውን በሁሉም መስክ እንዲያበረቱ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመርኀ ግብሩ ላይ የባንኩ ሴት ደንበኞች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።
