የዙሪያ ማሽን ፈላጊዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው

ዳሸን ባንክ፣ ኢትዮ ቴሌኮም እና ኤታ ሶሉሽንስ በጋራ የኢ.አር.ፒ፣ ፖስ እና ካሽ ሬጅስትር አገልግሎቶችን በአንድ ላይ ለመስጠት የሚያስችል “ዙሪያ” የተሰኘ የቢዝነስ አውቶሜሽን ሶሉሽን ይፋ ካደረጉ አንድ ወር ያስቆጠሩ ሲሆን፣ የዚህ የቢዝነስ መፍትሄ ማሽን ፈላጊዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡
አስካሁን ከ200 በላይ የሆኑ የተለያዩ ተቋማት (ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ፋብሪካዎች፣ ሱፐርማርኬቶች እና ሌሎች ቢዝነሶች) ዙሪያን መጠቀም የጀመሩ ሲሆን፣ እነዚህ ተቋማት በማሽኑ እንደ ቢዝነስ ጠባያቸው የቀረቡላቸውን አገልግሎቶች በስፋት እየተገለገሉባቸው ይገኛል፡፡
ዙሪያን እየተጠቀሙ ያሉ የቢዝነስ ሰዎች፣ “ማኔጀሮችና ካሸሮች” ከዚህ በፊት የሚጠቀሙበት የቢዝነስ አውቶሜሽን መንገድ የተበታታነና ለአስተዳደር የማይመች እንደነበር ገልፀው፣ ነገር ግን ዙሪያን መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ ሁሉንም የቢዝነስ ሂደቶች በቀላሉ ለመቆጣጠር እንዳስቻላቸው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ዙሪያ የንግድ ባለቤቶች በቀላሉ በእጅ ስልካቸው አማካኝነት የንግድ ቦታቸው መከፈቱን፣ በስቶክ ላይ ሁሉም እቃዎች ሙሉ መሆናቸውን፣ የተሸጡት እቃዎች የትኞቹ መሆናቸውን፣ማን እንደሸጣቸውና ሽያጩ ወደ ባንክ ገቢ መደረጉን ለመቆጣጠር እንዲችሉ አድርጓቸዋል፡፡
ለሰራተኞች ደግሞ ደንበኞች በተለያየ ማሽኖች የሚጠቀሙበትን አገልግሎት በአንድ ማሽን መመዝገብና ማስተናገድ እንዲችሉ ዕድል ከመፍጠሩ ባሻገር በራሱ በማሽኑ ክፍያ ጭምር ማስተናገድ አስችሏቸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ደንበኖች ክፍያ መፈፀም ሲፈልጉ የተለያየ የፖስ ማሽኖች ያስፈልግ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን ዳሸን ባንክ ከኤታ ሶልሽንስ ጋር ባመቻቸው ሲስተም የትኛውንም ካርድ በመቀበል ክፍያው ወደ ዳሸን ባንክ ገቢ እንዲሆን ይደረጋል፡፡