የደንበኞች ሳምንት ከዳሸን ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ደንበኞች ጋር ተከበረ
የዳሸን ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት (ሸሪክ) ደንበኞች፣ የባንኩ ሰራተኞችና የስራ ኃላፊዎች አምስተኛ ቀኑን ያስቆጠረውን የደንበኞች ሳምንት በባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት በድምቀት አከበሩ፡፡
በዓሉን የታደሙ የዳሸን ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ደንበኞች እንዳስታወቁት፣ ሁሉጊዜም ከዳሸን ባንክ (ሸሪክ) ጋር አብረው መስራታቸው ኩራተቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“ዳሸን ባንክ እንደቤታችን፣ እንደራሳችን፤ክፍተቶቻችንንም አብረን ተነጋግረን ተጋግዘን የምንሰራበት ቤት ነው፡፡ይህ የደንበኞች ሳምንት ከዓመት ዓመት እየተከበረ አብረን እንድንኖር ያድርግልን” ሲሉ ደንበኞች ገልጸዋል፡፡
የዳሸን ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ቺፍ ኦፊሰር አቶ መስፍን በዙ በበኩላቸው፣ በዚህ ሳምንት እየተከበረ የሚገኘው የደንበኞች ሳምንት የተለያዩ ጥሩ ተሞክሮዎችንና መልካም ልምዶችን ከማሳየቱ ባሻገር የተለያዩ መሻሻል ያለባቸውን አገልግሎቶች ከደንበኞች ለመስማት ዕድል መስጠቱን አስታውቀዋል፡፡
“ይህ የደንበኞች ሳምንት በየዓመቱ የምናካሂደው ጊዜያዊ መርሃ-ግብር ሳይሆን ከዚህ የምንወስዳቸውን መልካም ተሞክሮዎች ዓመቱን ሙሉ እያዳመጥን የምንዘልቅበትን፣ ከደንበኞቻችን ያገኘነውን ግብረ-መልስ ለእኛም አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል አጋዥ ሆኖን የምንቀጥልበት ሳምንት ነው፡” ሲሉ አቶ መስፍን አክለዋል፡፡
የዳሸን ባንክ ስትራቴጂ ቺፍ ኦፊሰር አቶ ኤልያስ ሁሴን በበኩላቸው የደንበኞች ሳምንት መርሃ- ግብሩ በርካታ ነገሮችን ያሳየና በባንኩ ሰራተኞችም ላይ መነሳሳትን ያመጣ መሆኑን ገልፀው፣ ሁሉም በርትቶና ጠንክሮ ዳሸን ባንክን አንድ እርምጃ የበለጠ እንዲስኬድ አደራ ብለዋል፡፡