Select Page

የዳሸን ባንክ 30ኛ ዓመት የምስረታ በዓል መከበር ጀመረ

የዳሸን ባንክ 30ኛ ዓመት የምስረታ በዓል መከበር ጀመረ

ከ30 ዓመት በፊት አሥራ አንድ ቅርንጫፎችን በአንድ ጀንበር ከፍቶ ሥራ በማስጀመር በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ የራሱን አሻራ ያሳረፈው ዳሸን ባንክ የምስረታ በዓሉን እኤአ ከጃንዋሪ 1 ቀን 2026 ጀምሮ ጀምሮ ለሚቀጥሉት ሶስት ወራት በተለያዩ ኹነቶች ማክበር ጀመረ፡፡

ዳሸን ባንክ የሦስት አሥርት ዓመታትን ያልተቋረጠ ስኬት ለሚዘክርበት ለዚህ በዓል የባንኩን ደንበኞች፣ ባለአክሲዮኖች፣የዳይሬክተሮች ቦርድና የማኔጅመንት አባላት፣ አጋር ተቋማትንና እንዲሁም ታታሪ ሰራተኞቹን እንኳን አደረሳችሁ ይላል፡፡

የዳሸን ባንክ የምስረታ በዓልን በማስመልከት መልዕክት ያስተላተላለፉት የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ዓለሙ “እንኳን ለዳሸን ባንክ 30ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አደረሳችሁ፤ዳሸን በኢትዮጵያ ገናና መለያ (ብራንድ) ባለቤት የኾነው ከምንም ተነስቶ በአጋጣሚ አይደለም ፡፡ዘመንን የሚሻገር ራዕይ የነበራቸው አሥራ አንድ መስራቾቹ በኢትዮጵያ እንደ ራስ ዳሸን ተራራ በሩቁ የሚታይ ትልቅ የፋይናንስ ተቋም ለመመሥረት በነበራቸው ቀና ፍላጎትና ፅኑ ዓላማ የተነሳ ነው ፡፡” ብለዋል፡፡

አቶ አስፋው አክለውም፣ ከጃንዋሪ 1 ቀን 2026 ጀምሮ ለሚቀጥሉት ተከታታይ ሦስት ወራት፤ ዳሸን ባንክ የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን ለማዘመን የነበረውን ፋና ወጊ ሚና፣ ለደንበኞቹ የገባውን ቃልኪዳን በመጠበቅ እንዲሁም በሦስት አሥርት ዓመታት ውስጥ ባንኩ ያለፈባቸውን ሂደቶች በማስታወስና በሁሉም መስክ ደማቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱትን የቀደሙ ባለውለታዎቹን በሚዘከሩ የተለያዩ ኹነቶች ያከብራል ፡፡

በ11 ባለአክሲዮኖች የተቋቋመው ዳሸን ባንክ በዚህ ወቅት የባለአክሲዮኖቹ ቁጥር 4,974 የደረሰ ሲሆን፣ በአስራ አንድ ቅርንጫፎች የተጀመረው የባንኩ አገልግሎት አሁን ላይ በ906 ቅርንጫፎች እየተሰጠ ይገኛል፡፡ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ከ14.9 ሚሊዮን ብር ተነስቶ በዚህ ወቅት 14.3 ቢሊዮን ብር ሆኗል ፡፡

የዳሸን ባንክ የተጠናቀቀው የበጀት ዓመት (2017) የፋይናንስ አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያሳየው የባንኩ ጠቅላላ ሃብት ከ254 ቢሊዮን ብር በላይ የተሻገረ ሲሆን፣ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ ደግሞ 202.2 ቢሊዮን ብር ሆኗል፡፡ በተጨማሪም የዳሸን ባንክ የደንበኞቹ ቁጥር ከስምንት ሚሊዮን በላይ ደርሷል፡፡

ለሚቀጥሉት ሶስት ወራት በተለያዩ ኹነቶች የሚከበረው የዳሸን ባንክ 30ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ባንኩ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ያለውን አበርክቶ በሚዘክሩ የተለያዩ ኹነቶች ይከበራል ፡፡

 

 

Facebook
Twitter
YouTube
LinkedIn
Instagram
Telegram