ዳሸን ባንክ ለረመዷን ወር ያዘጋጀዉን “ለ እናቴ” የሰደቃ መርሃ-ግብር በሻሽመኔ እና ጅማ ከተሞች አከናወነ
ዳሸን ባንክ ሸሪክ የረመዳን ወርን ምክንያት በማድረግ በሻሸመኔ እና ጅማ ከተሞች የኢፍጣር ማዕድ አጋርቷል።
የሐዋሳ ቀጠና ጽ/ቤት ዳይሬክተር አቶ አስናቀ ደምሴ በተገኙበት በመስጅዱ ሠላም ( አፖስቶ መስጅድ) በሻሸመኔ ከተማ ለሚገኙ አቅመ ደካማ ወገኖች የኢፍጣር ማዕድ ማጋራት ሥነ-ስርዓት አካሂዷል።
ለታላቁ የረመዳን ወር እንኳን አደረሳችሁ ያሉት አቶ አስናቀ “የተቀሩት የጾም ቀናቶች ዱዓችሁ ተቀባይነት የሚያገኝበት እንዲሆን እመኛለሁ” ብለዋል። ዳሸን ባንክ ማህበረሰብ-ተኮር ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
በተመሣሣይ መርሀ-ግብር ዳሸን ባንክ ጅማ ዲስትሪክት በጅማ ከተማ የረመዳን ወርን ምክንያት በማድረግ ለ50 አቅመ ደካሞች የባንኩ የስራ ኃላፊዎችና የከተማ አስተዳደሩ የመንግስት የስራ አመራሮች በተገኙበት የዘይት፣ዱቄትና ቴምር ድጋፍ ተደርጓል፡፡
የዳሸን ባንክ የጅማ ቀጠና ጽ/ቤት ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ በሻህ እንኳን ለታላቁና የተቀደሰው ረመዳን ወር በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል።
ዳይሬክተሩ አክለው “ረመዳን የመረዳዳት፣ የመተጋገዝና የመለገስ ወር ነው። ዳሽን ባንክ የሸሪዓህ ህግን መሰረት ያደረገ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለማህበረሰባችን እንደሚሰጥ ሁሉ፤ በማኅበራዊ ኃላፊነቱም ከጎናችሁ መቆምን እንደ ትልቅ ዕድል ይቆጥረዋል” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዳሽን ባንክ በጅማ ቀጠና ጽሕፈት ቤት አማካኝነት ወደፊትም እንዲህ ያሉ ማኅበራዊ ትብብሮችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል።
ድጋፍ የተደረገላቸው ወገኖችም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
