ዳሸን ባንክ ለደንበኞቹ የኢፍጣር መርሃ-ግብር አዘጋጀ
ዳሸን ባንክ የተከበረውን የረመዳን ወርን ምክንያት በማድረግ ለደንበኞቹ ልዩ የኢፍጣር መርሃ-ግብር በዛሬው ዕለት በሸራተን አዲስ ሆቴል አካሂዷል።
የኢፍጣር ዝግጅቱ ባንኩ ያለውን ማኅበራዊ ተሳትፎ ለማሳደግ እንዲሁም ከደንበኞቹ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር በማሰብ የተዘጋጀ ነው።
በዝግጅቱ ላይ የዳሸን ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው አለሙ ባደረጉት ንግግር ለባንኩ ደንበኞችና ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች መልካም የረመዳን ፆም ወቅት እንዲሆን ተመኝተዋል።አክለውም ዳሸን ባንክ ከደንበኞች እሴት እና የፋይናንስ ፍላጎት ጋር የሚጣጣሙ ሸሪዓዊ መርሆዎችን የሚያከብሩ የባንክ አገልግሎቶችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
ዳሸን ባንክ፣ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት (ሸሪክ) ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት ባለው ቁርጠኝነት መሰረት ባለፈው ዓመት ከደንበኞቹ በአደራ መልክ የሰበሰበውን ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ለ31 አገር-በቀል የግብረ-ሰናይ ድርጅቶች መለገሱ ይታወሳል።ከዚህ በተጨማሪም በሱማሌ ክልል ለሚገኙ ሴት ስራ ፈጣሪዎች ከወለድ ነጻ በሆነ መንገድ 100 ሚሊየን ብር ተዘወዋዋሪ ብድር ማቅረቡ ተጠቃሽ ነው፡፡
ካሉት አጠቃላይ ደንበኞች ከ1.5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት የወለድ ነፃ አገልግሎት ተገልጋይ የሆኑት ዳሸን ባንክ፣ ይኽንን የአብሮነትና ሁሉን አካታችነት እንዲሁም የለጋስነት ባህል ወደፊትም የሚያጠናክር ይሆናል፡፡
ባንኩ በአገር አቀፍ ደረጃ ለማህበረሰቡ ትርጉም ያለው አስተዋፅኦ የሚያበረክተውን፣ ሸሪዓህን መሰረት ያደረገውን፣ ደንበኞችን ያማካለ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ለማቅረብ ያለውን ተልዕኮ አጠናክሮ ይቀጥላል።
