ዳሸን ባንክ ልዩ የሱፐር አፕ ማስተዋወቅ ውድድር ሽልማትን ጨምሮ አራት አዳዲስ አገልግሎቶችን አስጀመረ
(አዲስ አበባ፡- መጋቢት 24፣ 2018 ዓ.ም)- ዳሸን ባንክ እስከ 6 ሚሊዮን ብር የሚያሸልም የሱፐር አፕ ማስተዋወቅ ውድድርን ጨምሮ በዓይነቱ ልዩ የሆነውን የዲጂታል ኦንቦርዲንግ አገልግሎት፣ ዳሸን ዳሸን ለወዳጄ (የዳሸን ስታር ሪፈራል) ፕሮግራም እንዲሁም ከማስተር ካርድ ጋር በመተባበር የተለያዩ ዓለም አቀፍ ክፍያዎችን መክፈል የሚያስችለውን የዳሸን ቨርቹዋል ካርድ አገልግሎትን በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቱ የንግድ ሥራ ትምህርት ቤት (ኮሜርስ) አስጀመረ፡፡
ዳሸን ባንክ የሱፐር አፕ ተጠቃሚዎችን ለማበረታት እንዲሁም የአገልግሎቱን ተደራሽነት ለማስፋት በማሰብ አጓጊ የቲክቶክ ይዘት ፈጠራ ውድድር (የሱፐር አፕ ክሬቲቭ አዋርድ) ያዘጋጀ ሲሆን፣ በዚህ ውድድር ለሚያሸንፉ የይዘት ፈጣሪዎች በድምሩ ስድስት ሚሊዮን ብር የገንዘብ ሽልማት አዘጋጅቷል፡፡
በዳሸን ሱፐር አፕ ቲክቶክ ቻሌንጅ አሸናፊ ለመሆን ይዘት ፈጣሪዎች ስለ ዳሸን ባንክ ሱፐር አገልግሎቶች የሚገልፅ የቲክቶክ ቪዲዮ በመስራት ማጋራት የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ የሰሩት ቪዲዮ በቲክቶክ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዕይታ ሲያገኝ፣ በዳሸን ሱፐር አፕ ውስጥ በሚገኘው የዳሸን ክሬቲቭ አዋርድ መተግበሪያ ድምፅ የሚሰጥበት ይሆናል፡፡በመጨረሻም ከፍተኛ ደምፅ በማግኘት አንደኛ ለሚወጣ ይዘት ፈጣሪ 3 ሚሊዮን ብር፣ ሁለተኛ ለሚወጣ 2 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ሶስተኛ ለሚወጣ ዳሸን ባንክ 1 ሚሊዮን ብር ይሸልማል፡፡
በዛሬው ዕለት ይፋ የተደረገው ሌላው አገልግሎት የዳሸን ስታር ሪፈራል ፕሮግራም ሲሆን፣ ይህ ፕሮግራም የዳሸን ሱፐር አፕ መተግበሪያ ተጠቃሚዎች በዙሪያቸው የሚገኙ ሰዎች እንዲጠቀሙበት በማድረግ የማበረታች ከፍያ እንዲያገኙ ለማስቻል የቀረበ አገልግሎት ነው፡፡በተለይም በተቀመጠው ደንብና ግዴታ መሰረት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የዳሸን ሱፐር አፕ መተግበሪያን አውርደው በአገልግሎት እንዲጠቀሙ የሚያደርጉ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የማበረታቻ ክፍያ ያገኛሉ፡፡
በዚህ ፕሮግራም ላይ ተሳታፊ ለመሆን ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች (ስታሮች) በቀላሉ https://referral-champion.dashensuperapp.com/dashboard በመግባት የሚመዘገቡ ሲሆን፣ በመቀጠል ምዘገባቸው ሲረጋገጥ ልዩ የሪፈራል ኮድ ያገኛሉ።
እነዚህ ስታሮች ልዩ ኮዳቸውን በማህበራዊ ሚዲያ፣ በኤስኤምኤስ፣ በኢሜል ወይም በአካል ሲያጋሩ የተላከለት ጓደኛ ወይም ግለሰብ የዳሸን ሱፐር አፕሊኬሽንን ያወርዳል፣ የላከለትን ስታር (ግለሰብ) ኮድ ያስገባል፣ እና ማንነቱን በተሳካ ሁኔታ በሚያረጋግጥ ጊዜ ስታሩ ለእያንዳንዱ ለተረጋገጠ አክቲቬሽን የማበረታቻ ክፍያ የሚያገኝ ይሆናል፡፡
ዳሸን ባንክ በኢትዮጵያ ባንኮች ውስጥ አዲስ ታሪክ የፈጠረውን የዲጂታል ኦን-ቦርዲንግ አገልግሎት በዛሬው ዕለት ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ይህ አገልግሎት አስተማማኝ እና ፈጣን የፋይዳ ብሄራዊ መታወቂያ በመጠቀም የባንክ ሒሳብ ለመክፈት የሚስችል በዲጂታል የሞባይል ባንክ አገልግሎት የቀረበ በአይነቱ አዲስ የሆነ አገልግሎት ነው፡፡
ዲጂታል ኦንቦርዲንግ በስልክ ቁጥር ብቻ የቨርቹዋል አካውንት የሚከፈትበት አገልግሎት ሲሆን፣ የፋይዳ መታወቂያ አገልግሎት መረጃዎችን በማረጋገጥ ደንበኞች በተለያዩ ደረጃዎች የተከፋፈሉ የተወሰኑ የባንክ አገልግሎቶችን እንዲገለገሉ ያስችላቸዋል፡፡ይህ አገልግሎት ከዚህ ቀደም የዳሸን ባንክ ሂሳብ አካውንት የከፈቱ ደንበኞች አካውንታቸውን ከዳሸን ሱፐር አፕ ጋር እንዲያጣምሩ ከማስቻሉ በላይ ንቁ የሱፐር አፕ ተጠቃሚ ያልሆኑ ደንበኞች ያለ ምንም ችግር ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው፡፡
በሌላ በኩል ከማስተር ካርድ ጋር በመተባበር የተለያዩ ዓለም አቀፍ ክፍያዎችን መክፈል የሚያስችለው የዳሸን ቨርቹዋል ካርድ አገልግሎት በዛሬው ዕለት ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ ይህ አገልግሎት በዳሸን ሱፐር አፕ ላይ የቀረበ የቨርቹዋል ካርድ ሲሆን፣ እንደ አሊባባ፣ አማዞን፣ ኔትፍሊክስን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ክፍያዎችን መክፈል ያስችላል፡፡
የዳሸን ባንክ ቨርቹዋል ካርድ ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ግብይቶች ክፍያን በቀላሉ መፈፀም ከማስቻሉም በላይ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚላክ ሃዋላ መቀበል የሚያስችል መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡ዳሸን ባንክ በቀጣይም ደንበኞች ስልካቸውን የፖስ ማሽን በማስነካት ብቻ በቨርቹዋል ካርዱ ክፍያ መፈፀም የሚችሉበትን አገልግሎት ይፋ የሚያደርግ ይሆናል፡፡
በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘው የዳሸን ሱፐር አፕ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎችን ያፈራ ሲሆን፣ በመተግበሪያው እስከ መጋቢት 2018 ዓ.ም በድምሩ ከ25 ሚሊዮን በላይ የገንዘብ ዝውውሮች ተደርገው ከ250 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የገንዘብ ዝውውሮች ተፈፅመዋል፡፡
ዳሸን ባንክ ሱፐርአፕ በርካታ አገልግሎቶችን በአንድ ማዕቀፍ ያካተተ ዘመናዊ፣ ፈጣንና አስተማማኝ አገልግሎት ማቅረብ የሚያስችል ሱፐር አፕ (መተግበሪያ) ሲሆን፣ ባንኩ በዚህ መተግበሪያ ለደንበኞች አገልግሎት ከማቅረብ ባሻገር እስከ 30 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ጠቅላላ የሽልማት ገንዘብ ያለው የዳሸን ዕድል ጨዋታን ለዳሸን ሱፐር አፕ ተጠቃሚዎች አቅርቧል፡፡