Select Page

ዳሸን ባንክ ስፖንሰር ያደረገው  ዐውደ-ርእይ በአዲስ ኮንቬንሽን ሴንተር ይከፈታል

ዳሸን ባንክ ስፓንሰር ያደረገውና በውበት እና ጤና አጠባበቅ ዙሪያ ላይ ያተኮረ ዐውደ-ርእይ (Radiance Fest 2025) የፊታችን ቅዳሜ በአዲስ ኮንቬንሽን ሴንተር ይከፈታል። ዐውደ-ርእዩን አስመልክቶ በትላንትናው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።

በጋዜጣዊ መግለጫው  ላይ ማብራሪያ የሰጡት የዳሸን ባንክ ተወካይ ወ/ሮ እስከዳር አሊ ባንኩ ከሚሰጣቸው ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶች ባሻገር ማህበረሰቡን በሚጠቅሙ ሁነቶች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ባንኩ “ዳሸን ካልቸር ክለብ” የተሰኘና ባህልና ኪነጥበባትን የሚደግፍ ክለብ በማቋቋም ዘርፉን በማነቃቃት እንዲሁም በማስተዋወቅ ረገድ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሆነም አንስተዋል።

በጤናው ዘርፍ ታላቁ ሩጫን በመደገፍ እና ተያያዥ ሁነቶችን በማገዝ ባንኩ የድርሻውን እየተወጣ እንደሆነም ወ/ሮ እስከዳር ገልፀዋል።

በቀጣይ ጥቅምት 22 እና 23/2018 በአዲስ ኮንቬንሽን ሴንተር  የሚከፈተው የውበት አጠባበቅ ላይ የሚያተኩረው (Radiance Fest 2025) ላይ የጤናና የውበት መጠበቂያ ምርቶች የሚተዋወቁበትና የፓናል ውይይቶች የሚከናወኑበት መድረክ ነው።

በዝግጅቱ ላይ መሳተፍ የሚፈልጉ በዳሸን ባንክ ሱፐር አፕ የመግቢያ ትኬት መቁረጥ እንደሚችሉ በወቅቱ ተገልጿል።

የሁነቱ አዘጋጅ የሆነው ፍሎውለስ ኢቨንትስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዩአዳን ጥላሁን በበኩላቸው የውበት ጤና አጠባበቅ መስክ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰፊ ትኩረት የተሰጠው እንደሆነ አስረድተዋል። በቀጣዩ ሁነትም ዘርፉ ያለውን ዕድገትና  አቅም አስመልክቶ ለታዳሚዎች ክፍት የሆነ መድረክ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል። የዝግጅቱ ዓላማ ሀገር በቀል የጤናና ውበት አጠባበቅ እንዲሁም ምርቶችን ማስተዋወቅ እንደሆነም ተገልጿል።

Facebook
Twitter
YouTube
LinkedIn
Instagram
Telegram