ዳሸን ባንክ በአጋርነት ያዘጋጀው የአፍሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ እየተካሄደ ይገኛል
የመጀመሪያው የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ (ASMIS 2026) ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።
ዳሸን ባንክ ስፖንሰር ያደረገውና በፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ እንዲሁም በኤጂኤ ቴክ ኢንተርፕራይዝ የጋራ ትብብር የተዘጋጀው ይህ ጉባኤ የአፍሪካን በተለይ የኢትዮጵያን እውነተኛ ገጽታ ለዓለም ለማስተዋወቅ ያለመ ነው።
በዳሸን ባንክ ቺፍ ስትራቴጂ ኦፊሰር አቶ አየለ ተሾመ ዳሸን ባንክ የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ ከአገር ባለፈ አህጉርን በማስተዋል ረገድ ሚናው ከፍ ያለ እንደሆነ አንስተዋል።
ዳሸን ባንክ ይህን በጎ ዓላማ በመደገፍ በጉባኤው ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆኑን የገለጹት አቶ አየለ ዘመኑ የዲጂታል እንደመሆኑ ባንኩ ከዘመኑ ጋር የሚሄዱ አገልግሎቶችን እያስተዋወቀ ይገኛል ብለዋል።
ተወዳጅነቱ ከፍ እያለ የመጣውን ዳሸን ሱፐር አፕ መተግበሪያ ጨምሮ ሌሎች ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶች በጉባኤው ላይ እየተዋወቁ እንደሆነም አብራርተዋል።
የፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍጹምእሸት ሽመልስ በበኩላቸው ዳሸን ባንክ ይህ ደማቅ ጉባኤ ስኬታማ እንዲሆን ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
መሰል ጉባኤዎች ያሉንን መልካም ገጽታዎች በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም ተናግረዋል።
ዳሸን ባንክ በቅርቡ እስከ 6 ሚሊዮን ብር የሚያሸልም የዳሸን ባንክ ክሬቲቭ ቻለንጅን የማስተዋወቅ ውድድርን ጨምሮ በዓይነቱ ልዩ የሆነውን የዲጂታል ኦንቦርዲንግ አገልግሎት፣ የዳሸን ለወዳጄ ሪፈራል ፕሮግራም እንዲሁም ከማስተር ካርድ ጋር በመተባበር የተለያዩ ዓለም አቀፍ ክፍያዎችን መክፈል የሚያስችለውን የዳሸን ቨርቹዋል ካርድ አገልግሎትን ማስተዋወቁ ይታወሳል።
በጉባኤው ከ30 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 61 ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ተሳታፊ ሲሆኑ ግለሰቦቹ በድምሩ 321 ሚሊየን የሚጠጋ ተከታይ አላቸው።
ከዚህ ባለፈ በድምሩ 150 ሚሊየን ተከታዮች ያላቸው 120 ኢትዮጵያውያን የይዘት ፈጣሪዎችም በጉባኤው አዲስ የዲጂታል ታሪክ ለመጻፍ እየተካፈሉ ነው።
