Select Page

ዳሸን ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ የመጀመሪያውን ሱፐር አፕ ለአገልግሎት አቀረበ

ጋዜጣዊ መግለጫ
 
(አዲስ አበባ: ጥር 06: 2017 ዓ.ም)- ዳሸን ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የመጀመሪያ የሆነውንና በርካታ አገልግሎቶችን በአንድ ማዕቀፍ ያካተተ ዘመናዊ፣ ፈጣንና አስተማማኝ አገልግሎት ማቅረብ የሚያስችል ሱፐር አፕ (መተግበሪያ) በሸራተን አዲስ ሆቴል አስመርቋል፡፡
 
የዳሸን ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ዓለሙ ባደረጉት ንግግር ‘’ዳሸን ባንክ ሱፐር አፕ የበለጠ አቅም ይፈጥርልናል፡፡ በሁሉም የስራ ዘርፎች ለተሰማሩ ደንበኞቻችን ይበልጥ አሰተማማኝ፣ ጥራት ያለውና ውጤታማ አገልግሎት በመስጠት ደንበኛ-ተኮር አገልግሎት ለመስጠት ያስቀመጥነውን ራዕይ ይበልጥ ዕውን ለማድረግ ያስችለናል” ብለዋል፡፡ ዳሸን ባንክ ሱፐር አፕ የባንኩን ዲጂታል የባንክ አገልግሎቶች አንድ እርምጃ ወደፊት የሚወስድ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
 
አቶ አስፋው ዳሸን ባንክ ከዋና ዋና አጋሮች ጋር በመተባበር አዳዲስ፣ ዘመናዊ እና አስተማማኝ የዲጂታል ባንክ አገልግሎቶችን ማቅረቡን ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል፡፡
 
ዳሸን ባንክ ሱፐርአፕ በዲጂታል ባንኪንግ ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መተግበሪያ ነው፡፡ ለአጠቃቀም ምቹና ለእይታም ማራኪ የሆነው መተግበሪው በግል ሂሳብ እና ለተለያዩ የቢዝነስ ተቋማት አገልግሎት መስጠት እንዲያስችል ሆኖ የቀረበ ነው፡፡
 
ሁሉን በአንድ ያቀፈ የባንክ አገልግሎት፡ ይህ ሱፐር አፕ በርካታ አገልግሎቶችን ያካተተ ሲሆን አካውንቶችን መክፈት፣ ከአካውንት ወደ አካውንት በፍጥነት ገንዘብ ማስተላለፍ፣ እንዲሁም በገንዘብ ልውውጥ ላይ የተመሰረተ የብድር አገልግሎት መስጠትና ሌሎች አገልግሎቶችን በአንድ የያዘ መተግበሪያ ነው፡፡
 
ትክክለኛ የደንበኞች መረጃ፡ ይህ ሱፐር አፕ የደንበኞችን ማንነትና በህይወት መኖራቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል በመሆኑ ከዚህ ጋር ተያይዞ የነበረውን ክፍተት በማስቀረት ባንኩ የተረጋገጠ የደንበኞች መረጃ እንዲኖረው ያስችላል፡፡
ለሁሉም ደንበኛ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል፡
 
ደንበኞች በአዲሱ ሱፐር አፕ ከመደበኛ የባንክ አገልግሎት በተጨማሪ በሸሪዓህ ህግ መሰረት የቀረቡ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቶችን ማግኘት ይችላሉ፡፡
 
ሌላው በዚህ ሱፐር አፕ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚቀርበው አገልግሎት ደንበኞች የግል ወጪያቸውን መምራት የሚችሉበት “በጀት” የተሰኘ አገልግሎት ነው፡፡ ይህ አገልግሎት ደንበኞች ለተለያዩ ዕለታዊ፣ ወርሃዊና አመታዊ ወጪዎቻው የመደቡትን የተለያየ በጀት በመከታተል ያለበትን ደረጃ ስለሚያሳውቅ የፋይናንስ አጠቃቀማችንን በአግባቡ ለመምራት ያግዛል፡፡
 
ዳሸን ሱፐር አፕ ካካተታቸው አዲስ አገልግሎቶች ሌላኛው ደንበኞች በሶስት ንክኪ ብቻ (Three Click Shopping) የተለያዩ ምርቶችና አገልግሎቶችን በፍጥነትና አመቺ በሆነ መልኩ መገብየት የሚያስችለው ነው፡፡ ዳሸን ባንክ ሱፐር አፕ በሌላው አለም እንደሚታወቁት አማዞንና አሊባባ ነጋዴዎች ምርታቸውን በሱፐር አፑ በማቅረብ መሸጥ የሚችሉበት ዕድል ይፈጥራል፡፡ የዚህ ግብይት ተጠቃሚዎች ክፍያቸውን በዳሸን ሱፐር አፕ አካውንታቸው በኩል በቀላሉ በመፈፀም መገበያየት ይችላሉ፡፡
 
ይህ ሱፐር አፕ ደንበኞች ዲጂታል ካርድ ወይም ቨርቹዋል ካርድ በማውጣት ከፕላስቲክ ካርዶች የተሻለ ፈጣንና አስተማማኝ አገልግሎት እንዲያገኙም አማራጭ አቅርቧል፡፡ ዳሸን ባንክ ሱፐር አፕ ደንበኞች በፍጥነት በኪው አር ኮድ አማካኝነት ክፍያ እንዲፈጽሙ እና ገንዘብ እንዲለዋወጡ የሚያስችል ነው፡፡
 
ዳሸን ባንክ ሱፐር አፕ በውስጡ በርካታ የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት የሚችሉ መተግበሪያዎች ያካተተ በመሆኑ ደንበኞች ሌላ የአገልግሎት አማራጮችን መክፈት ሳያስፈልጋቸው በዚህ ሱፕር አፕ በርካታ አገልግሎቶችን በፍጥነት ማግኘት ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ የአየር ትኬት ለመቁረጥና ተያያዥ አገልግሎቶችን ለማግኘት፣ በቴሌቲቪ አማካኝነት የአገር ውስጥ ፊልሞች ለመመልከት፣ የዲሴስቲቪ አገልግሎቶችን ለማግኘትና ሌሎች በርካታ አገልግሎቶችን ማግኘት የሚያስችሉ መተግበሪያዎችን ያካተተ ነው፡፡
 
እስካሁን ያልነበረና ለአገራችን የባንክ አገልግሎት ዘርፍ የመጀመሪያ የሆነውና በዚህ ሱፐር አፕ የተካተተው አገልግሎት “ቻት ባንኪንግ” ይሰኛል፡፡ ይህ አገልግሎት ደንበኞች በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ በስልካቸው የፅሁፍ መልዕክት በመለዋወጥ ገንዘብ በፍጥነት መላላክ ያስችላል፡፡ ይህን አገልግሎት ለመጠቀም ሁለቱም ገንዘብ የሚላላኩ ደንበኞች የዳሸን ሱፐር አፕ ተጠቃሚ መሆን አለባቸው፡፡
 
በዳሸን ሱፐር አፕ የተካተቱ በርካታ አገልግሎቶች በቅደም ተከተል የሚቀርቡ ሲሆን በሁለተኛው ምዕራፍ ደንበኞች በሱፐር አፑ በሚያደርጉት አጠቃላይ የገንዘብ ልውውጥ ላይ የተመሰረት አነስተኛ የብድር አገልግሎት በቀጥታ ማግኘት ያስችላቸዋል፡፡
 
በዚሁ ምዕራፍ ደንበኞች ካላቸው ተቀማጭ ገንዘብ ቀንሰውና የሚቆጥቡበትን የጊዜ ገደብ ራሳቸው ወስነው ካዝና ውስጥ ተቀማጭ በማድረግ የወለድ ክፍያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዕድል የሚሰጥ አገልግሎትም የሚጀምር ይሆናል፡፡
 
ዳሸን ባንክ የተለያዩ ፈር ቀዳጅ የባንክ ዘርፍ ቴክኖሎጂዎችን በተደጋጋሚ ያስተዋወቀ ሲሆን አሁን ለአገልግሎት ያበቃው ዳሸን ባንክ ሱፐት አፕ በርካታ አዳዲስ የአገልግሎት አማራጮችን ለባንክ ኢንዱስትሪው በማስተዋወቅ ባንኩ ይበልጥ ዘመናዊ አገልግሎት መስጠት የሚችልበት አማራጭ ይሆናል፡፡

 

 

      

Facebook
Twitter
YouTube
LinkedIn
Instagram
Telegram