ዳሸን ባንክ በዓለም አቀፉ ኢስላሚክ ፋይናንስ ጉባኤ ላይ ተሳተፈ
ዳሸን ባንክ ከወለድ ነጻ አገልግሎት(ሸሪክ) አባል የሆነበት የዓለም አቀፉ ኢስላሚክ ፋይናንስ እስታንዳርድ አውጭ ድርጅት በባህሬን ማናማ ባዘጋጀው 23ተኛ የሸሪዓ ቦርድ ጉባኤ ላይ ተሳትፏል፡፡
የድርጅቱ የሸሪዓ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ሼይኽ ሙፍቲ ሙሐመድ ተቂይ ኡስማኒ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ከመላው ዓለም ጉባኤው ላይ ለመሳተፍ የመጡ እንግዶችን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል፡፡
በጉባኤው ላይ የዳሸን ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የሸሪዓ ቦርድ አማካሪ ልዑካን በጉባዔው ላይ የተሳተፈ ሲሆን ዓለም አቀፍ ልምድና ተሞክሮዎችን እንደወሰደ ተመላክቷል፡፡
በዳሸን ባንክ የሸሪዓ አማካሪ ኮሚቴ ጸሃፊና በባንኩ የሸሪዓ ኮምፕሊያንስና ግምገማ ከፍተኛ ስራ አስኪያጅ አቶ መሐመድ ይመር ለሁለት ቀናት የቆየው ጉባኤ ከወለድ ነጻ በሆነው የፋይናንስ ዘርፍ ላይ እየታዩ ያሉ ለውጦችና ተግዳሮቶችን በተመለከተ ሰፊ ምክክር እንደተደረገና ምክረ ሃሳብም እንደተሰጠበት ተናግረዋል፡፡
በጉባኤውም ላይ የዘርፉ ምሁራን ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበው ውይይት የተደረገም ሲሆን፤ በኢስላሚክ ፋይናንስ የህግ ማእቀፍ አስተዳደር፣ በዘርፉ ብቁ የሠው ሃይልን በበቂ ሁኔታ ማፍራት እንደሚገባና እና በሌሎች የኢስላሚክ ባንክ ፕሮዳክቶችና አግልግሎቶች ዙሪያ ሰፋ ያለ ውይይት መደረጉን አቶ መሐመድ አብራርተዋል፡፡
የዳሸን ባንክ የሸሪዓ ኮሚቴ አማካሪዎች ከጉባኤው ጎን ለጎን በተደረጉ የሁለትዮሽ ግንኙነቶች ከተለያዩ ሀገራት ከመጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ጋር በኢስላሚክ ፋይናንስ ዘርፍ ያሉ አዳዲስ አሰራሮችንና ሌሎች ተሞክሮዎችን እንደቀሰሙም ተናግረዋል፡፡
የሸሪዓ ቦርድ አማካሪው ካገኘው ልምድ በመነሣት ለባንኩ በቀጣይም ድጋፍ እንደሚያደርግ አመላክተዋል፡፡ ይህ ደግሞ የባንኩን ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የበለጠ ለማጠናከርና ለማሳደግ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡
ከጉባኤው በኢንዱስትሪው ዙሪያ በርካታ ግብዓቶች የተገኙበት እንደሆነም አቶ መሐመድ አክለው ገልጸዋል፡፡
ባንኩ በዓለም አቀፍ ደረጃም The Accounting and Auditing Organization for Islamic Financial Institutions (AAOIFI) ቋሚ አባል ነው።