ዳሸን ባንክ አክሲዮን ማህበር የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ምዝገባና የደንበኛ ሳቢ መግለጫን ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ – (ታህሳስ 16፣ 2018) —
የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን (ECMA) የዳሸን ባንክ አክሲዮን ማህበርንን በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ውስጥ ለመሳተፍ የሚያስችለውን የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ምዝገባ መግለጫ ማፅደቁን አስታወቀ።
የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ማረጋገጫ ተከትሎ፣ ዳሸን ባንክ የደንበኛ ሳቢ መግለጫ (Prospectus) እና ተዛማጅ ገላጭ ሰነዶችን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ እነዚህም ሰነዶች በባንኩ ይፋዊ ድረ-ገፅ (www.dashenbanksc.com) ላይ ለሕዝብ ቀርበዋል።
የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን የምዝገባ መግለጫውን ማፅደቁ ባንኩ ለምዝገባ የሚያስፈልጉትን መረጃዎችና ሰነዶች በተገቢው መንገድ ማሟላቱን ያሳያል።
የዳሸን ባንክ የአክሲዮን ሽያጭ የደንበኛ ሳቢ መግለጫው ስለ ባንኩ የፋይናንስ አገልግሎቶች፣ የፋይናንስ አፈፃፀም መረጃዎች፣ ተጠባቂ ስጋቶች፣ የአክሲዮን ባለቤትነት ቅድመ ሁኔታዎች ዝርዝር መረጃ የሚሰጥ ሲሆን፣ ይህም በቀጣይ ለህዝብ የሚቀርቡትን አክሲዮኖች የሚገዙ ተሳታፊዎች በመረጃ ላይ የተመሰረተ ግምገማ እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል።
ባንኩ ወደዚህ ወሳኝ ምዕራፍ መሸጋገሩን በተመለከተ አስተያየት የሰጡት የዳሸን ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ዓለሙ “የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የምዝገባ መግለጫችንን ማፅደቁ ለዳሸን ባንክ ትልቅ ምዕራፍ ሲሆን፣ በግልጽነት፣ በመልካም አስተዳደር እና በሕግ ማክበር ላይ ያለንን ጠንካራ ቁርጠኝነት ያሳያል። ይህ ወሳኝ እርምጃ ዘላቂ እድገት እና የረጅም ጊዜ እሴት የሚፈጥሩ ሁኔታዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በካፒታል ገበያው ላይ ተሳታፊ ለመሆን ያለንን ዝግጁነት ያጠናክራል።” ብለዋል።
ዳሸን ባንክ በሰነደ ሙዓለ ንዋይ (አክሲዮን) ተሳታፊ ለመሆን ፍላጎት ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ማንኛውንም የኢንቨስትመንት ውሳኔ ከማድረጋቸው በፊት የደንበኛ ሳቢ መግለጫውን (Prospectus) እና ተያያዥ ሰነዶችን ሙሉ በሙሉ እንዲያነቡ ጥሪ ያቀርባል።በተያያዘም ፍላጎት ያላቸው ዜጎች በተፈቀደላቸው የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ደላሎች ጋር በመቅረብ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ (አክሲዮን) ሂሳብ (አካውንት) እንዲከፍቱ ባንኩ ያበረታታል።
ይህ ማስታወቂያ ለመረጃ አገልግሎት ብቻ የተዘጋጀ ሲሆን ማንኛውንም ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ለመግዛት ወይም የግዢ ጥያቄን ማቅረብን አይመለከትም። ማንኛውም ለህዝብ የሚቀርቡ የአክሲዮን ሽያጮች በደንበኛ ሳቢ መግለጫና ተዛማጅ ሕግናና ደንቦች መሠረት ይሆናል።