Select Page

ዳሸን ባንክ ከአክሲዮን (Accion) እና ማስተር ካርድ ጋር በመተባበር አነስተኛ ቢዝነሶች  ዲጂታል ኢኮኖሚን እንዲቀላቀሉ የሚያግዝ የኢኖቬሽን የልህቀት ማዕከል ለማቋቋም ስምምነት አደረጉ

በኢትዮጵያ ግንባር ቀደም የግል ባንክ የሆነው ዳሸን ባንክ ለትርፍ ካልተቋቋመው ዓለም አቀፍ ድርጅት አክሲዮን (Accion) እና ማስተርተካርድ ሴንተር ፎር ኢንክሉሲቭ ግሮውዝ ጋር በመተባበር የአነስተኛ ቢዝነሶችን የፋይናንስ ፍላጎት በዲጂታል አገልግሎት ለማሟላት የሚያሰችል አዲስ የኢኖቬሽን የልህቀት ማዕከል ለማቋቋም ስምምነት አደረጉ፡፡

በዚህ ስምምነት መሰረት አክሲዮን ዳሸን ባንክ ለጥቃቅን አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራዞች የዲጂታል ባንክ አገልግሎትና በተለይም በሴቶች ባለቤትነት የሚመሩ ቢዝነሶችን ለመደገፍ ለሚያቋቁመው የኢኖቬሽን ልህቀት ማዕከል ግንባታ ድጋፍ የሚያደርግ ይሆናል፡፡

በኢትዮጵያ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ የአነስተኛ፣ መካከለኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ኢኮኖሚውን በማንቀሳቀስ ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ሲሆኑ ነገር ግን ከዚህ ውስጥ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑት 1.9 በመቶ አነስተኛ እና 6 በመቶ ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ብቻ ናቸው፡፡በአገሪቱ በጥቃቅን አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራዞች  ዘርፍ ያለው የፋይናንስ ክፍተት 4.2 ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን ይገመታል።ሥራ አጥነት፣ አነስተኛ ገቢ እና የፋይናንስ ግንዛቤ እጥረት ለመደበኛ የፋይናንስ አገልግሎት እጦት ቁልፍ ምክንያቶች ሆነው ቆይተዋል።ከዚህም በላይ 55 በመቶ ከሆነው የወንዶች ድርሻ ጋር ሲነፃፀር በመደበኛ የፋይናንስ ተቋም ውስጥ የባንክ ሂሳብ (አካውንት) ያላቸው ሴቶች 39 በመቶ ብቻ ሲሆኑ ይህም እያደገ በመጣው የዲጂታል ፋይናንስ ስነ-ምህዳር እንዳይጠቀሙ ከማድረጉም በላይ እና ለአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ ገድቦታል፡፡

ዳሸን ባንክ በኢትዮጵያ አዳዲስ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ ግንባር ቀደም ሆኖ ቆይቷል።በተለይም የአነስተኛ ቢዝነስ ባለቤቶች እንከን አልባ የገንዘብ ልውውጥ እንዲያደርጉ የሚያግዛቸውን የዲጂታል ዋሌት በቅድሚያ ካስተዋወቁ ባንኮች ዳሸን ቀዳሚው ነው፡፡አሁንም ከአክሲዮን ጋር በመሆን የሚገነባው የኢኖቬሽን ልህቀት ማዕከል በዋናነት ዓላማ ያደረገው በኢትዮጵያ በተለምዶ በጥሬ ገንዘብ ላይ ተንጠልጥለው አገልግሎታቸውን የሚያቀርቡትንና ጥቂት ንብረቶች ያላቸው በተለይም በትላልቅ ባንኮች ዕይታ ውስጥ ላልገቡ የአነስተኛ፣ መካከለኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች አዳዲስ መፍትሄ ለማቅረብ ነው፡፡

የዳሸን ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው አለሙ እንዳሉት “አነስተኛ ቢዝነሶች ለአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ቢያደርጉም በተለይም በሴቶች የሚመሩ አነስተኛ የንግድ ተቋማት ከፍተኛ የፋይናንስ ፈተናዎች ይገጥሟቸዋል። ይህም የሆነበት ምክንያት በአብዛኛው በጥሬ ገንዘብ ላይ የተመሰረቱ ግብይቶች ላይ በመመስረትን የንግድ ሥራቸው በቂ ባልሆነና መደበኛ የፋይናንስ መዛግብት ሳይጠቀሙ በመስራታቸው እንዲሁም ሴቶች በንብረት ላይ የባለቤትነት መብት በማጣት የመያዣ መስፈርቶችን ካለማሟላት ጋር የሚያያዝ ነው።በዚህ አጋርነት እነዚህን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ፣ የዳሸን ባንክን የአገልግሎት አቅም ለመገንባት፣ የብድር አቅርቦቶቻቸንን በማሻሻል የአነስተኛ የንግድ ባለቤቶችን ፍላጎት ለማሟላት እንዲሁም የተለያዩ ዲጂታል አገልግሎቶችንና ንግዶቻቸውን በተሳካ ሁኔታ ለማሳደግ የሚያስፈልጋቸውን ግብዓቶች እንዲያገኙ የሚያስችል የንድፈ ሃሳብ አገልግሎት ድጋፍ ለማድረግ የምንረባረብ ይሆናል፡፡

የዳሸን ባንክ ቺፍ ዲጂታል እና ኢንፎርሜሽን ኦፊሰር አቶ ዮሃንስ ሚሊዮን እንደተናገሩት፣ ዳሸን ባንክ ስድስተኛውን የስትራቴጂክ ዕቅድ ቀርፆ ወደ ስራ ሲያስገባ ከያዛቸው አበይት ተግባራት(Initiatives) አንዱ የኢኖቬሽን ልህቀት ማዕከል መገንባትና የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች (Medium and Small Enterprises-MSME) አገልግሎቶችን የማቅረብ አቅም መጨመር ነው ብለዋል።በተጨማሪም ይህ የባንኩ እርምጃ የፋይናንስ አካታችነት እንዲሁም የፈጠራ አገልግሎት የታከለባቸውን የዲጂታል አገልግሎቶችን በማቅረብ ኢኮኖሚን መገንባትን የሚለውን አላማ ያደረገ ነው ብለዋል።

የጋራ ስምምነቱን መሰረት በማድረግ አክሲዮን፣ በተለይም ዳሸን ባንክ የአነስተኛ፣ መካከለኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችን ታሳቢ አድርጎ የሚያቀርባቸውን አዳዲስ አገልግሎቶች ሰው ሰራሽ አስተውህሎ (Artificial Intelligence-AI) በመጠቀም በተለይም በሴቶች ባለቤትነት የሚተዳደሩ ቢዝነሶች ምቹ የሆነ አዲስ የብድር አመዘጋገገብ ሞዴል እንዲኖራቸው ለማዘጋጀት ይረዳል፡፡ይህንን የተመዘገበ መረጃና ጥናትን መሰረት በማድረግ አዲስ የሚገነባው የኢኖቬሽን ልህቀት ማዕከል  ቢዝነሶች ከብድር አቅራቢ ደንበኞቻቸው እንደ ብድር ያሉ መፍትሄዎችን ለማቅረብ፣ አካታች የቢዝነስ አገልግሎቶች፣ ፋይናንስ ነክ ያልሆኑ እንደ የቢዝነስ አስተዳደር ያሉ መፍትሄዎችን ለማገዝ የሚረዳ ይሆናል፡፡

ዳሸን ባንክ በዚህ ወቅት የኢኖቬሽን ልህቀት ማዕከሉን ዕውን ለማድረግ ጨረታ አውጥቶ፣ አስፈላጊውን የግንባታ ቅድመ ዝግጅት አጠናቋል።ይህ ፈር ቀዳጅ ግንባታ “ሁልጊዜ አንድ እርምጃ ቀዳሚ” ብሎ የተነሳውን ባንክ ቁርጠኝነት ከማሳየት ባሻገር በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ያለውን የቀዳሚነትና ፈርቀዳጅነት ሚና የሚያጠናክር ይሆናል።በቀጣይ ለባንኩ ከፍተኛ አመራሮችና ሰራተኞች የኢኖቬሽን ወርክሾፕ የሚዘጋጅ ሲሆን፣ በተለይም አርቴፊሻል  ኢንተለጀንስን ጨምሮ ወቅቱ ያፈራቸው ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀምን በተመለከተ ከዓለም አቀፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያው አብሮ ለመስራት ታቅዷል ብለዋል።

የአክሲዮን ምክትል ፕሬዚዳንት እና የመካከለኛው ምስራቅ እና አፍሪካ አማካሪ የሆኑት ራሊያት ሱሞኑ አንዳሉት፣ “ኢትዮጵያ በአፍሪካ በፍጥነት በማደግ ላይ ካሉ ኢኮኖሚዎች አንዷ ነች እና ትናንሽ ቢዝነሶች ደግሞ ይህንን እድገት በማስፋፋት ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።በዚህ ትብብር በፋይናንስ ኢኖቬሽን ውስጥ መሪ ከሆነው ከዳሸን ባንክ እና ሌሎች ስትራቴጂክ አጋሮች ጋር በመተባበር  በኢትዮጵያ ውስጥ ለጥቃቅን አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራዞች የበለጠ አካታች ሥነ-ምህዳር ለመገንባት የምናግዝ ይሆናል። በጋራ በመሆን በተለይም በሴቶች የሚመሩ ኢንተርፕራይዞችን አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና ሌሎች የቴክኖሎጂ አማራጮችን በማቅረብ ተግባራዊ የምናደርግ ይሆናል።

Facebook
Twitter
YouTube
LinkedIn
Instagram
Telegram