ዳሸን ባንክ ከኤሌጋንስ አስመጪ እና ላኪ ድርጅት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ
ዳሸን ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት (ሸሪክ) እና ኤሌጋንስ አስመጪና ላኪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
በስምምነቱ መሠረትም ባንኩ በትራንስፖርትና የተለያዩ የንግድ ዘርፎች ተሰማርቶ ለሚገኘው ኤሌጋንስ አስመጪና ላኪ ድርጅት ለሜትር ታክሲ ትራንስፓርት አገልግሎት ለሚያውላቸው የመጀመሪያ ዙር እስከ 50 የሚደርሱ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ መኪናዎች ግዢ ከወለድ ነጻ በሆነ መንገድ ፋይናንስ ያመቻቻል፡፡
የዳሸን ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ተጠባባቂ ቺፍ ኦፊሰር አቶ አምዱ ሰማን በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ወቅት እንዳብራሩት ስምምነቱ ዳሸን ባንክና ኤሌጋንስ አስመጭና ላኪ ድርጅት ያላቸውን ግንኙነት በተሻለ ለማሳደግ የሚያግዝ ነው፡፡
ባንኩ በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ የያንጎ ትራንስፖርት ቢዝነስ ለመስራት ልዩ ፈቃድ ካለው ኤሌጋንስ አስመጭና ላኪ ጋር የፈጸመው የመግባቢያ ስምምነት በሜትር ታክሲ ትራንስፓርት ዘርፍ የስራ ዕድሎችን ከፍ ለማድረግ እንደሚያግዝ አመላክተዋል፡፡
በተጨማሪም ፋይናንስ የሚደረጉት የኤሌክትሪክ ተሸርካሪዎች የአካባቢ ጥበቃን ማዕከል ያደረጉ በመሆናቸው ባንኩ ለአካባቢና ማህበረሰብ ደህንነት የሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡
የኤሌጋንስ አስመጪና ላኪ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቶፊቅ መሐመድያሲን በበኩላቸው ዳሸን ባንክ በድርጅታቸው ላይ ላሳደረው ዕምነትና የፋይናንስ አቅርቦት ምስጋናቸውን ገልጸው፤ ድርጅታቸው ከዳሸን ባንክ ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
ስምንተኛ ዓመቱን እያከበረ የሚገኘው ሸሪክ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ1.5 ሚሊዮን በላይ የተሻገረ ሲሆን አጠቃላይ ሃብቱ ደግሞ ከ26 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡