Select Page

ዳሸን ባንክ ከኤምፔሳ-ሳፋሪኮም እና ካሽ ጎ ጋር በመተባበር ዓለም አቀፍ የሐዋላ አገልግሎት ማቅረብ ጀመረ

ዳሸን ባንክ ከኤምፔሳ-ሳፋሪኮም እና ካሽ ጎ ጋር በመተባበር ዓለም አቀፍ የሐዋላ አገልግሎት ማቅረብ ጀመረ

በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሐዋላ አገለግሎትን በማቀላጠፍ ግንባር ቀደም የሆነው ዳሸን ባንክ ከኤምፔሳ-ሳፋሪኮም እና ካሽ ጎ ጋር ስምምነት በማድረግ ዓለም አቀፍ የሐዋላ አገለግሎትን መስጠት ጀመረ፡፡

ጥር 29 ቀን 2017 ዓ.ም በዳሸን ባንክ ዋና መስሪያ ቤት በተደረገው የሶስትዮሽ የስምምነት መርሃ ግብር ይህ አዲስ አገልግሎት ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ስምምነቱ የሐዋላ ገንዘብ ልውውጥን አስተማማኝና ቀልጣፋ ለማድረግ ትልቅ ሚና ይጫወታል ተብሏል።

ይህ አገልግሎት ይፋ መደረጉን ተከትሎ ለደንበኞች ከጥር 29 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ወራት የሚቆይ የ10 በመቶ ልዩ የማበረታቻ ስጦታ የቀረበ ሲሆን፣ይህም ደንበኞች ከውጭ አገራት ገንዘብ ሲልኩ በዕለቱ ካለው ምንዛሬ የ10 በመቶ ተጨማሪ ጉርሻ ያገኛሉ፡፡ በተጨማሪም ካሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የአንድ ጌጋ ባይት ነፃ የኢንተርኔት አገልግሎት ይበረከትላቸዋል፡፡

የዳሸን ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ተወካይና ቺፍ ሬቴይል እና ኤም ኤስ ኤም ኢ ኦፊሰር አቶ ይህንዓለም አቅናው እንዳስታወቁት፣ ዳሸን ባንክ፣ከኤምፔሳ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እና ካሽ ጎ ጋራ ስምምነት አድርገው ያቀረቡት ዓለም አቀፍ የሃዋላ አገልግሎትን ሊያሳልጥ የሚችል አውታር ይፋ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ዳሸን ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ትልቅ ስም ያለው የንግድ ተቋም ነው ያሉት አቶ ይህንዓለም፣ ባንኩ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖው በጎ አስተዋፅኦ ማድረግ የቻለና በዚህም የሚታወቅ መሆኑን ጠቁመው ፣ በ29 ዓመታት ጉዞው ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያለው ሃብት የሚያስተዳደድር ተቋም መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የዓለም አቀፍ ንግድን በመደገፍ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ያለው ዳሸን ባንክ በተለይም የሐዋላ አገልግሎትን በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከማቀላጠፍ አኳያም ግንባር ቀደም ሚና ሲጫወት መቆየቱ ተገልጿል፡፡

ዳሸን ባንክ ከብዙ የሐዋላ ሰጪ ተቋማት ጋር የሚሰራ ቢሆንም ከካሽ ጎ እና ከኤምፔሳ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ጋር በጥምረት ያቀረበው አገልግሎት ለየት የሚያደርገው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተፅኖ እየፈጠሩ ከመጡ ተቋማት ጋር የቀረበ መሆኑን አቶ ይህንዓለም ተናግረዋል፡፡አክለውም ዳሸን ባንክ ከተቋማቱ ጋር በመሆን በጎ ተፅዕኖ መፍጠር የሚቻልበትን ዕድል የሚፈጥር እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡

የዳሸን ባንክ ቺፍ ዲጂታል እና ኢንፎርሜሽን ኦፊሰር አቶ ዮሃንስ ሚሊዮን በበኩላቸው፣ሐዋላ ለአገር የሚያበረክተውን አስተዋፅ አስረድተው በዚህም ዳሸን ባንክ ከ ኤምፔሳ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እና ካሽ ጎ ጋር በመሆን ያቀረበው የሐዋላ አገልግሎት በቀላሉ የካሽ ጎን መተግበሪያን በመጠቀም የኤምፔሳን አማራጭ በመምረጥ የውጭ አገራት ገንዘብ በማስገባት በአጭር ጊዜ ገንዘብ የሚተላለፍበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኤም-ፔሳ ሳፋሪኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ኤልሳ ሙዞሊኒ ስምምነቱን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር የትብብር ስምምነቱ የፋይናንስ አካታችነትን ለማበረታታት እና አዳዲስ የዲጂታል የፋይናንስ መፍትሄዎችን ለማቅረብ ተቋማቸው ካለው ተልዕኮ ጋር የሚጣጣም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የሶስቱ ተቋማት ስምምነት ኢትዮጵያውያን ከውጭ በቀጥታ በካሽ ጎ ሞባይል አፕልኬሽን አማካይነት ወደ ኤምፔሳ ገንዘብ የሚላክበትና መቀበል የሚቻልበትን ዕድል የሚፈጥር ይሆናል፡፡

 

Facebook
Twitter
YouTube
LinkedIn
Instagram
Telegram