ዳሸን ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ሸሪክ ማህበረሰቡ ላይ ያተኮሩ ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ
ዳሸን ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ሸሪክ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሴሚናር አካሄደ።
ሴሚናሩን በንግግር የከፈቱት በዳሸን ባንክ ነቀምቴ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ አስፋው ብርሐኑ የሴሚናሩ ተሳታፊዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል።
ዳሸን ባንክ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፎችን በመክፈት ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎቱን በተሻለ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የዳሸን ባን የሸሪዓ አማካሪ ኮሚቴ አባል ሸህ ሰኢድ ኪያር በበኩላቸው ዳሸን ባንክ በሸሪዓዊ መርሆዎችን ያከበሩ አገልግሎቶች ተደራሽ እንዲሆኑ ትኩረት የሚሰጥ ባንክ እንደሆነ አስረድተዋል።
ዳሸን ባንክ ሸሪክ ጠንካራ የሸሪዓ አማካሪ ኮሚቴ እንዳለው ያነሱት ሸህ ሰኢድ ኪያር ሸሪክ ዜጎች በነጻነት የባንክ ተጠቃሚ ሆነው ለሐገር የተሻለ አበርክቶ እዲኖራቸው እየሰራ ነው ብለዋል።
በዳሸን ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ አለባቸው ወጋ በበኩላቸው ሸሪክ የሚሰጣቸውን አገልገሎት በክልሉ ለማስፋትና ለማጠናከር እንደሚሰራ አመላክተዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ፕሬዝደንት ሐጂ ኢብራሂም ሙሐመድ ዳሸን ባንክ በክልሉ የተጠናከሩ ስራዎችን እንዲሰራ የክልሉ እስልምና ጉዳዮች የበኩሉን እንደሚወጣ ገልጸዋል።
ክልሉ ካለው አቅም አንጻር ዳሸን ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎቱን ማስፋፋት እንዳለበትም ሐጂ ኢብራሂም ጠቅሰዋል።
ሸሪክ የሚሰጣቸውን ማህበረሰብ ተኮር አገልግሎቶችና አለም አቀፍ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ተመክሮዎችን በተመለከተ በባንኩ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የስራ ሐላፊዎች ማብራሪያ ተሰጥቷል።
በሴሚናሩ ላይ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥተዋል።
