ዳሸን ባንክ ከ22 ሚሊየን ብር በላይ ለግብረ-ሠናይ ድርጅቶች ለገሰ
ዳሸን ባንክ ከ22 ሚሊየን ብር በላይ ለግብረ-ሠናይ ድርጅቶች ለገሰ
°ከወለድ ነፃ አገልግሎት 7ኛ ዓመት ተከበረ
ዳሸን ባንክ ከደንበኞቹ በአደራ የሰበሰበውን ከ22 ሚሊየን ብር በላይ ለተለያዩ አገር-በቀል ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ለገሰ፡፡ ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት (ሸሪክ) የጀመረበትን 7ተኛ ዓመት ዛሬ በተለያዩ መርሃ-ግብሮች በዋናው መስሪያ ቤት አክብሯል፡፡
በዳሸን ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ቺፍ ኦፊሰር አቶ መስፍን በዙ ሸሪክ በሚል ስያሜ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የጀመረበትን 7ተኛ ዓመት ባከበረበት ዕለት ባደረጉት ንግግር አመኔታቸውን ለሠጡ ደንበኞች የላቅ ምስጋና እናቀርባለን ሲሉ ተናግረዋል።
ባንኩ በሚሰጠው ከወለድ ነፃ አገልግሎት ብቻ በአሁኑ ወቅት ከ1 ሚሊየን በላይ ደንበኞች ማፍራት ችሏል።
ዳሽን ባንክ የካቲት 26/2010 በአንድ መስኮት የጀመረው አገልግሎት አድጎ ከ80 በላይ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ቅርንጫፎችና ከ800 በላይ በሆኑ ቅርንጫፎች በመስኮት ለደንበኞቹ የተሟላ የባንክ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
በዛሬው ዕለት ለ 31 አገር-በቀል ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል፡፡
ዳሸን ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት በሱማሌ ክልል ለሚገኙ ሴት ስራ ፈጣሪዎች ከወለድ ነጻ በሆነ መንገድ 100 ሚሊየን ብር ተዘወዋዋሪ ብድር ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ በዛሬው ዕለትም ይህን ድጋፍ አስመልክቶ ዘጋቢ ፊልም ለዕይታ ቀርቧል፡፡
የባንኩ ከወለድ ነፃ አገልግሎት (ሸሪክ) እ.ኤ.አ ህዳር 28 ቀን 2023 በባህሬን ማናማ በተካሄደው 9ኛው የኢስላሚክ ሪቴል ባንክ ሽልማት ላይ ጠንካራ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በኢትዮጵያ የሚሠጥ ባንክ (The Strongest Islamic Retail Banking Window in Ethiopia ) በሚል ዕውቅና አግኝቷል፡፡
ዕውቅናውን የሰጠው ለንደን በሚገኘውና በፋይናንስ ዘርፍ ጥናትና ምርምር የሚሰራው ኬምብሪጅ አይ ኤፍ ኤ(Cambridge IFA) የተሰኘ ተቋም ነው፡፡
ባንኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ የእስላማዊ ፋይናንስ ተቋማቶችን የሂሳብ፣ ኦዲት እና ሸሪዐህ መስፈርቶችን የሚያወጣው ተቋም (The Accounting and Auditing Organization For Islamic Financial Institutions) አባል የሆነ በኢትዮጵያ ብቸኛው የፋይናንስ ተቋም ነው።