ዳሸን ባንክ ዓመታዊ የደንበኞች ሣምንትን እያከበረ ይገኛል
ዳሸን ባንክ ዓመታዊ የደንበኞች ሳምንትን በተለያዩ መርሃ-ግብሮች እያከበረ ይገኛል፡፡
የባንኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ የደንበኞች ሣምንት ደንበኞች ከባንኩ ጋር ላላቸው አጋርነት ክብርና እውቅና ለመስጠት ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የደንበኞች ሣምንት፤ደንበኞች የባንኩ ሕልውና እና መሠረት መሆናቸውን ለመመስከርና ደንበኛን ማዕከል ያደረገ አገልግሎት የመስጠት ዕሴታችንን አጉልተን ለማሣየት የምናከብረው ነው ብለዋል፡፡
ባንኩ ከአፍሪካ ምርጥ ባንኮች ውስጥ አንዱ ሆኖ የመገኘት ራዕዩን ለማሳካት የሚችለው በላቀ የደንበኞች አገልግሎት እንደሆነ የጠቆሙት አቶ አስፋው የባንኩን የስኬት ጉዞ ለማረጋገጥ ጊዜው የሚጠይቀውን የሙያ ብቃትና ተነሳሽነት አስቀጥሎ እንደሚጓዝም አብራርተዋል፡፡
አሁን ላይ ባለው ተለዋዋጭ ዓለም በባንክ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚስተዋለው ውድድር ውስብስብና ጠንካራ እንደሆነ ያነሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው እያንዳንዱን ቀን በትጋትና በቁርጠኛነት በመስራት ገበያው የሚፈጥራቸውን ተግዳሮቶች ወደ ዕድል መለወጥ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡
ዓመታዊ የደንበኞች ሣምንት እየተከበረባቸው ከሚገኙ የባንኩ ቅርንጫፎች መካከል አንዱ የሆነው አሙዲ ቅርንጫፍ ሲገለገሉ ያገኘናቸው ደንበኞች በበኩላቸው ዳሸን ባንክ ደንበኛን ያከበረ መስተንግዶ እየሰጠ እንደሆነ ተናረዋል፡፡
ባንኩ ከጊዜ ወደ ጊዜ አገልግሎቱን በማሻሻል አመርቂ ስራ እያከናወነ እንደሆነ የሚገልጹት ተገልጋዮች ደንበኞች በአካል ቀርበው ከሚያገኙት አገልግሎት ባሻገር በዲጅታል ባንኪንግ ዘርፍ አዳዲስ አማራጮችን እያቀረበ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡