Select Page

ዳሸን ባንክ ደንበኞቹን አመሰገነ

ዳሸን ባንክ “ሰላሳ ዓመታትን በአብሮነት” በሚል መሪ ሐሳብ ሲያካሂድ የነበረው የደንበኞች ሣምንት የመዝጊያ መርኅ-ግብር በዋናው መስሪያ ቤት አከናወነ።

የዳሸን ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ ባደረጉት ንግግር  ደንበኞችን አመስግነው ለመርኅ- ግብሩ ስኬታማነት የባንኩ የስራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ሊመሰገኑ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ዝግጁቱ ለአንድ ዓላማ አንድነትና ጠንካራ ትብብር የታየበት እንደሆነ ያነሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው ከደንበኞች የተገኙ ግብረ መልሶች ለባንኩ መራሔ-ዕቅድ መሳካት ወሳኝና ወደ ተግባር ሊቀየሩ የሚገባቸው ናቸው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው አስረድተዋል።

ከደንበኞች የተገኙ ገንቢ ሐሳቦችን ወደ ተግባር ለመቀየር ቁርጠኛ መሆን ይገባናል ያሉት አቶ አስፋው ለዚህ ደግሞ ከሁሉም ኃላፊነቶች ይጠበቃሉ ብለዋል።

ዳሸን ባንክ ከክቡራን ደንበኞቹ ያገኛቸው ግብረ-መልሶች ባንኩ ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጣቸውና ለተጨባጭ ለውጥ እንድንሰራ ያበረታታናል ሲሉ አስረድተዋል።

በመርኅ-ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት በዳሸን ባንክ የከስተመር ሰርቪስ ቺፍ ኤክሲፒሪየንስ ኦፊሰር እየሩሳሌም ዋጋው በበኩላቸው  የደንበኞች ሣምንት ለባንኩ ደንበኞች ያለውን አክብሮትና ምስጋና ለማቅረብ ታልሞ የተዘጋጀ እንደሆነ ተናግረዋል።

ለአስር ቀናት በተለያዩ መሰናዶዎች ሲከናወን በቆየው የደንበኞች ሣምንት ለባንኩ ደንበኞች ዕውቅና የተሰጠበትና ባሉበት ጉብኝት የተደረገበት እንደሆነም ጠቁመዋል።

በደንበኞች ሣምንት መርኅ-ግብር የባንኩን የረጅም ዓመት ደንበኞች ግንኙነታቸውን የበለጠ እንዲያጠናክሩ እንዲሁም አዳዲስ ደንበኞች ጋር በቀጣይ በጋራ ለመስራት የሚቻልባቸው አጋጣሚዎች የተፈጠረበት እንደሆነም አብራርተዋል።

በጉብኝቱ ተሳታፊ የነበሩ የባንኩ ሰራተኞች በደንበኛ ጉብኝት ወቅት ያጋጠማቸውን ተመክሮ አጋርተዋል።

የዳሸን ባንክ የደንበኞች ሣምንት ከመስከረም 5- 15/2018 ዓ.ም በደማቅ ሁኔታ ሲከናወን ቆይቷል።

 

 

 

Facebook
Twitter
YouTube
LinkedIn
Instagram
Telegram