Select Page

ዳሸን የገዘፈ ስሙን ተጠቅሞ ደንበኞች የሚተማመኑበት ባንክ ሆኖ እንደሚቀጥል አስታወቀ

አንድ እርምጃ ወደ ፊት ቀድሞ የሚገኘው ዳሸን ባንክ ይህንን ግዙፍ ስም እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ደንበኞች የሚተማመኑበት ባንክ ሆኖ እንደሚቀጥል አስታወቀ፡፡

ይህ የተገለፀው ከጥር 20-25 ቀን 2017 ዓ.ም በታላቅ ድምቀት ሲከበር የቆየው የዳሸን ባንክ የደንበኞች ሳምንት የመዝጊያ ሥነ ስርዓት በባንኩ ዋና መስሪያ ቤት በተከናወነበት ወቅት ነው፡፡

የዳሸን ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ዓለሙ በመርሃ-ግብሩ ለተገኙ የባንኩ ደንበኞች፣የባንኩ ከፍተኛ አመራሮችና ሰራተኞች ባደረጉት ንግግር ምንም ፈታኝ ነገሮች ቢኖሩም ለዳሸን ባንክ መጪው ጊዜ ብሩህ ተስፋ ያለው መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

የዳሸን ባንክ ደንበኞች ሳምንት ሲከበር የተለያዩ እንቅስቀሴዎች ሲከናወኑ እንደነበር ያስታወሱት አቶ አስፋው፣ ጥር ለባንኩ ትልቅ ወር እንደሆነ፣ ይህም ትልቅ ራዕይ ያላቸው 11 ባለሃብቶች ሃብታቸውን አውጥተው ዳሸን ባንክን የመሰረቱበት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ዳሸን ባንክ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ዕድገቱን እየተከተለ መሪ ቃሉን ሲቀይር ሁለት ነገሮች ታሳቢ እንሚደረጉ ያብራሩት አቶ አስፋው፣እነዚህም ደንበኞችና ደንበኞች የሚስተናገዱበት ስልት ቴክኖሎጂን መርህ ያደረገ እንዲሆን የሚሉት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

“ደንበኛን ማመስገን” በሚል ቃል ሲከበር የቆየውን ይህንን ልዩ የደንበኞች ሳምንት በዳሸን ባንክ በዋናነት ለማክበር ያስፈለገው ደንበኞችን ለማክበር፣ ለማመስገንና አልፎ ተርፎም ቤተሰብ ሆነው የተወዳጁት ደንበኞች በአገልግሎቱ ያላቸውን ገንቢ አስተያየት ለመቀበል መሆኑን አቶ አስፋው ገልጸዋል፡፡

የዳሸን ባንክ የደንበኞች ሳምንት የባንኩን ሰራተኞች ከመቼውም ጊዜ በላይ አገልግሎት የመስጠት ተነሳሽት ያሳየ ሲሆን፣ ይህም በመላው አገሪቱ በሚገኙ ከ800 በላይ በሆኑት የባንኩ ቅርንጫፎች ተረጋግጧል፡፡

መርሃ-ግብሩ በደመቀ መልኩ ተጀምሮ የተጠናቀቀ ሲሆን ደንበኞችንም ያነቃቃ ነበር።

ሌላው በመርሃ-ግብሩ ጎልቶ የታየው የዳሸን ባንክ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን ብዝሃነት በሚያሳየ መልኩ የተገነባ መሆኑ መንጸባረቁ ነው፡፡በቀጣይም ይህ የዳሸን ባንክ የደንበኞች ሳምንት የማይቋረጥና የባንኩ ዓመታዊ ኹነት ሆኖ የሚከበር መሆኑ ታውቋል፡፡

 

Facebook
Twitter
YouTube
LinkedIn
Instagram
Telegram