Select Page

ዳሸን ባንክ በቴክኖሎጂ የታገዘ የዱቤ ግብይት አስተዋወቀ

(አዲስ አበባ፡ ታህሳስ 25፤2015) ዳሸን ባንክ በቴክኖሎጂ የታገዙ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ በሚሊየን የሚቆጠሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የባንክ አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ባንኩ አዳዲስ አገልግሎቶችን የማስተዋወቅ ጥረቱን በመቀጠል አሁንም ከኤግል ላየን ቴክኖሎጂስ ጋር በመተባበር የቆየውን የማህበረሰባችንን የዱቤ ግብይት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና አስተማማኝ የባንክ አሰራር በማገዝ ዱቤ አለ የተሰኘና ሸማቾች በዱቤ በፈለጉት ጊዜ ያሻቸውን ገዝተው ቆይተው መክፈል የሚችሉበትን አሰራር እና መተግበሪያ ጥር 02 ቀን 2015 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ሆቴል አስመርቋል፡፡

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የዳሸን ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙን ጨምሮ በርካታ የንግድ ማህበረሰቡ ተገኝተዋል፡፡

ይህ አገልግሎት ዳሸን ባንክ ከተለያዩ የንግድ ተቋማት ጋር በመተባበር ህብረተሰቡ ቋሚና አላቂ ዕቃዎችንና በርካታ አገልግሎቶችን በ3 ወር፣ በ6 ወርና በ12 ወር በሚመለስ ዱቤ በወለድና ያለወለድ መግዛት የሚያስችል አማራጭ ነው፡፡ ይህም የማህበረሰባችንን የኑሮ ጫና ይቀንሳል፤ በገበያው ውስጥ ምርት እንዲገላበጥ፣ አገልግሎቶችም ይበልጥ ጥቅም ላይ እንዲውሉ እና የንግድ ማህበረሰቡ ሽያጭ እንዲያድግ ብሎም ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

ዱቤ አለ የምርትና አገልግሎት አቅራቢዎች ለደንበኞቻቸው እጅግ አመቺ የሆነ የዱቤ አገልግሎት በማቅረብ ተመራጭነታቸውን እንዲያሳድጉም ይረዳል፡፡

ደንበኞች መተግበሪያውን ከፕሌይ ስቶር ወይም ከአፕ ስቶር በማውረድ ለአገልግሎቱ መመዝብ ይችላሉ፡፡ ከተመዘገቡ በኋላም ወደ ዳሸን ባንክ ቅርንጫፍ በማምራት የዱቤ ገደብ ማስፈቀድና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ፡፡

ዳሸን ባንክ ጠንካራ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት መገንባት የቻለ ሲሆን በቅርቡ በግል ባንኮች ታሪክ የመጀመሪያው ትልቅና ዘመናዊ የሆነውን የመረጃ ማዕከል አስመርቋል፡፡ በዚህ ጠንካራ መሰረተ ልማት ላይ ተንተርሶም አሞሌ በተሰኘው የዲጂታል ባንክ አገልግሎቱ ሰፊውን የማህበረሰባችን ክፍል ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ በቅርቡም አነስተኛ ቁጠባና ብድር ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር መጀመሩ ይታወሳል፡፡

 

Facebook
Twitter
YouTube
LinkedIn
Instagram
Telegram