Select Page

ዳሸን ባንክ ዘመናዊ የመረጃ ማዕከል አስመረቀ

(ሰኔ 16 /2014፣ አዲስ አበባ) በኢትዮጵያ የባንክ አገልግሎት ታሪክ ውስጥ የአዲስ ዘመን ጅማሮ ተደርጎ ሊወሰዱ የሚችሉትን የኤሌክትሮኒክ ክፍያ እና የሞባይል ካርድ አገልግሎቶች በማስተዋወቅ ረገድ ፈር ቀዳጅ የሆነው ዳሸን ባንክ፣ ዘመናዊና በግል የፋይናንስ ተቋም ደረጃ የመጀመሪያ የሆነውን Tier III የመረጃ ማዕክል አስመረቀ፡፡

የመረጃ ማዕከሉ ከፍተኛ ኃይል ያላቸውን ከ1,000 ያላነሱ ሰርቨሮችና ሌሎች ተያያዥ የኔትወርክ መሳሪያዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው ነው፡፡ በጥገና ወቅትም መደበኛ የባንኩን ስራ ሳያቋርጥ አመቱን ሙሉ አገልግሎት መስጠት የሚችል ነው፡፡

የመረጃ ማዕከሉ በአካባቢው የሚስተዋሉ የተለያዩ ክስተቶችን በመለየት ለማዕከሉ ዋና የመቆጣጠሪያ ክፍል መረጃ ማስተላለፍ የሚችል ሲሆን፣ ችግር ሲከሰትም ችግሩን በመለየት ስጋቶችን ለማስቀረት በሚችል ዓለማቀፋዊ ደረጃውን የጠበቀ ቴክኖሎጂ የተሟላ ነው፡፡

ይህ የመረጃ ማዕከል ዘመናዊ የባንክ አገልግሎትን ከየትኛውም ቦታ ማግኘት የሚያስችልና ባንኩ የተለያዩ አዳዲስ አገልግሎቶችን ያለምንም ችግር ወደ ስራ ለማስገባት የሚያግዘው ይሆናል።

በተጨማሪም ባንኩ በዲጂታል ዘርፍ አዳዲስ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅና የአገልግሎቱንም ደህንነትና ጥራት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ሁነኛ ሚና ይኖረዋል።

ይህ ማዕከል የዳሸን ባንክን ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር በስራ ላይ ለሚገኙ እና ወደ አገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ለሚቀላቀሉ የአገር ዉስጥም ሆነ የዉጭ ባንኮች እንዲሁም ለሌሎች ተቋማት አገልግሎት መስጠት የሚችል አቅም ያለዉ ነዉ፡፡

በዳታ ማዕከሉ ምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ የብሔራዊ ባንክ ገዢ፣ የባንኮች ስራ አስፈፃሚዎች፣ የተለያዩ ድርጅት ኃላፊዎች፣ የባንኩ የስራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የባንኩ የበላይ አመራሮች፣ ተገኝተዋል።

 

Facebook
Twitter
YouTube
LinkedIn
Instagram
Telegram