Select Page

ዳሸን ባንክ የ10 ቢሊየን ብር ገቢ ይፋ አደረገ

  • ባሳለፍነው በጀት አመት 2.4 ቢሊየን ብር ትርፍ አስመዝግቧል
(ህዳር 09 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ) ዳሸን ባንክ ባለፈዉ በጀት አመት 10 ቢሊየን ብር አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱን ይፍ አደረገ፡፡ ባንኩ በበጀት አመቱ ከግብር በፊት 2.4 ቢሊየን ብር ትርፍ አስመዝግቧል፡፡

የዳሸን ባንክ አ.ማ ዓመታዊ 28ኛ መደበኛና 25ኛ ድንገተኛ ጉባኤ ህዳር 09 ቀን 2014 ዓ.ም በመቻሬ ሜዳ ተካሂዷል፡፡ በጉባኤዉ ላይ ያለፈዉ የበጀት አመት አፈፃፀምና የዚህ ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች ተነስተዉ ዉይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በጉባኤዉ ላይ ያለፈዉን ዓመት አፈፃፀም ዉጤት ያቀረቡት የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ንዋይ በየነ ያለፈዉ የበጀት አመት በርካታ ተግዳሮቶች የተስተዋሉበት እንደነበር አስታዉሰዋል፡፡ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተከሰተዉ ጦርነትና የኮሮና ቫይረስ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖዎችንም ለአብነት አንስተዋል፡፡ በሌላ በኩል የገንዘብ ኖት ለዉጡ ወደባንኮች የሚመጣዉን የገንዘብ መጠን የመጨመርና ሌሎች አዉንታዊ ሚናዎችን መጫወቱን አመልክተዋል፡፡

ዳሸን ባንክ የተከሰቱትን ፈታኝ ሁኔታዎች በመቋቋም በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቡን የገለፁት አቶ ንዋይ በበጀት አመቱ 21.1 ቢሊየን ብር ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰብ መቻሉንና የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ 74.6 ቢሊየን የደረሰ መሆኑን አዉስተዋል፡፡ ይህም ካለፈዉ ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ39.4 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡ የባንኩ አጠቃላይ የሃብት መጠንም 94.7 ቢሊየን ብር የደረሰ ሲሆን ይህም ከቀደመዉ ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ38.7 በመቶ የላቀ ነዉ፡፡ የባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ባለፈዉ በጀት ዓመት ከፍተኛ ዕድገት ያስመዘገበ ሲሆን በአጠቃላይ ባንኩ ለሰበሰበዉ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 4.8 ቢሊየን ብር አበርክቷል፡፡ በተጠናቀቀዉ በጀት አመት የባንኩበ ደንበኞች ቁጥር ከሶስት ሚሊየን በላይ ሲሆን የአሞሌ ተጠቃሚዎች ቁጥር 2.4 ሚሊየን ደርሷል፡፡

ባንኩ በመተግበር ላይ ያለዉን የአምስት ዓመት ሰትራቴጂ ዕቅድ ካለዉ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በሚጣጣም መልኩ ማሻሻሉንም አቶ ንዋይ አመልክተዋል፡፡ ዕቅዱ ባንኩን ይበልጥ ተወዳዳሪ፤ ትርፋማ እና ቀጣይነት ያለዉ ዕድገት እንዲያስመዘግብ በሚያስችል መልኩ መከለሱንም ጠቁመዋል፡፡ያለፈዉ ዓመት ባንኩ 25ኛ ዓመቱን በተለያዩ መርሃግብሮች ያከበረበት በመሆኑ ታሪካዊ ነበርም ብለዋል፡፡

የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋዉ ዓለሙ ባንኩ ባለፈዉ አመት 10.3 ቢሊየን ብር አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱንና 7.8 ቢሊየን ብር ወጭ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡

ዳሸን ባንክ ከአፍሪካ ቀዳሚ ባንኮች አንዱ ለመሆን የሰነቀዉን ራዕይ ለማሳካት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

ባንኩ ቁጠባን ለማሳደግ፣ በክፍያ ካርድ የታገዘ ዘመናዊ ግብይትን ለማበረታታት አና ዓለም አቀፍ ሃዋላን አና ክፍያን ለማሳለጥ የሚረዱ አዳዲስ አገልግሎቶችን ማስተዋወቁ ተገልጿል፡፡

አቶ አስፋዉ ባንኩ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ከመወጣት አንጻር ገበታ ለሃገር፤ የአካባቢ ጥበቃና የአቅመ-ደካሞች ምገባ መርሃግብር እና ለሌሎች መልካም ተግባራት ድጋፍ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡

   

Facebook
Twitter
YouTube
LinkedIn
Instagram
Telegram