Select Page

ዳሸን ባንክ 6.4 ቢሊየን ብር ትርፍ አስመዘገበ

ዳሸን ባንክ ባለፈው በጀት ዓመት ብር 6.4 ቢሊየን ትርፍ ማስመዝገቡን ገለጸ፡፡ የባንኩ ባለአክሲዮኖች 31ኛ መደበኛና 26ኛ አስቸኳይ ጉባኤ በሚሊንየም አዳራሽ ዛሬ የተካሄደ ሲሆን ያለፈው ዓመት የባንኩ የስራ አፈፃፀም፣ የዚህ በጀት ዓመት እቅድና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የዳሸን ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ዱላ መኮንን ባለፈው በጀት ዓመት በባንክ ኢንዱስትሪው አውንታዊና አሉታዊ ሁኔታዎችን የፈጠሩ አለም አቀፋዊና አገራዊ ክስተቶች እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡

አቶ ዱላ ባለፈው በጀት አመት በኢትዮጵያ የነበረው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት፣ በተለያዩ ቦታዎች የቀጠሉ ግጭቶችና የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እጥረት በባንክ ኢንዱስትሪው ላይ የበኩሉን አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን አስገንዝበዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የዳሸን ባንክ ተቀማጭ የገንዘብ መጠን የ30.9 ቢሊየን ብር እድገት ማስመዝገቡንና የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን 145.9 ቢሊየን ብር መድረሱን አቶ ዱላ አውስተዋል፡፡ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ ለባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ያበረክተው ድርሻ 11.1 ቢሊየን ብር እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡

የዳሸን ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ዓለሙ በበኩላቸው የባንኩ አጠቃላይ ሃብት ባለፈው በጀት ዓመት የ27 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ብር 183.7 ቢሊየን መደረሱን ገልፀዋል፡፡ ባንኩ ባለፈው በጀት ዓመት 1.44 ሚሊየን አዳዲስ ደንበኞችን ማግኘት እንደቻለና ይህም ለባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ ዕድገት የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከቱን ገልፀዋል፡፡ ባንኩ በአሁኑ ወቅት ከ6.7 ሚሊየን በላይ ደንበኞች እንዳሉትም ተመልክቷል፡፡

Facebook
Twitter
YouTube
LinkedIn
Instagram
Telegram