ዳሸን ባንክ በሸገር ከተማ አስተዳደር ለሚገኙ ሴት ተማሪዎች ዳግም ጥቅም ላይ የሚውል የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ አደረገ

ዳሸን ባንክ ከሃንስ ዊዝ ኬር ድርጅት ጋር በመተባበር በሸገር ከተማ አስተዳደር ለሚገኙና የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ የመግዛት አቅም ለሌላቸው ከ1,500 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች ዳግም ጥቅም ላይ የሚውል የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ አደረገ፡፡
የማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በየዓመቱ የተለያዩ ድጋፎችን የሚያደርገው ዳሸን ባንክ በተለይም ሴቶችን ለመደገፍ የሚያከናውነው የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ድጋፍ ይጠቀሳል፡፡
ለአብነትም ባለፉት ዓመታት ከሐንስ ዊዝ ኬር ጋር በመተባበር በደሴ፣ወልዲያ፣ ኮምቦልቻ፣አክሱም፣ መቐለ፣አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ለሚማሩና ድጋፍ ለሚሹ ሴት ተማሪዎች በድምሩ ከ8,000 በላይ ዳግም ጥቅም ላይ የሚውሉ የንጽሕና መጠበቂያዎችን አስረክቧል።
ዘንድሮም በንጽህና መጠበቂያ እጥረት ምክንያት በርካታ ሴት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንዳይቀሩ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ፣ ዳሸን ባንክ በሸገር ከተማ አስተዳደር ለሚገኙና የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ የመግዛት አቅም ለሌላቸው ከ1,500 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የሸገር ሲቲ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት የርክክብ ሥነ ስርዓት አከናውኗል፡፡
ሐሙስ መስከረም 15 ቀን 2018 ዓ.ም በሸገር ከተማ አስተዳዳር ከንቲባ ጽ/ቤት በተደረገው የርክክብ ሥነ ስርዓት የተገኙት የአስተዳደሩ ከፍተኛ ሥራ ሃላፊዎች ዳሸን ባንክ ስላደረገው ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

