አዲስ አበባ-ህዳር 10-2016 ዓ.ም፡ ዳሸን ባንክ የአለም አቀፉ አነስተኛና መካከለኛ ተቋማት ፋይናንስ ፎረም (SME Finance Forum) አባል መሆኑን ድርጅቱ ባወጣው ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ አመልክቷል፡፡ የፎረሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ ቀመር ሳሊም በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ ቀዳሚ ከሆኑት ባንኮች አንዱ የሆነውን ዳሸን ባንክን አባል በማድረጉ ፎረሙ በጣም ደስተኞ መሆኑን ገልፀው ባንኩ በአለም አቀፍ ደረጃ አነስተኛና መካከለኛ ተቋማትን ለመደገፍና የፋይናነስ አገልግሎቶችን ይበልጥ እንዲያገኙ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝም ገልፀዋል፡፡ ፎረሙ በአነስተኛና መካከለኛ ተቋማት ላይ አተኩረው በሚሰሩ ተቋማት መካከል ትስስር ለመፍጠርና የዕውቀት፣ የፈጠራ፤ የመልካም ተሞክሮዎች፣ የፖሊሲ ሽግግሮች እንዲኖሩ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የዳሸን ባንክ ቺፍ ስትራቴጂና ኢኖቬሽን ኦፊሰር አቶ ሙሉጌታ አለባቸው በበኩላቸው ዳሸን ባንክ የፎረሙ አባል በመሆን በአለም አቀፍ የአነስተኛና መካከለኛ ፋይናንስ ዘርፍ ያለውን ቦታ ይበልጥ ለማጉላት፣ በዘርፉ ካሉ ተቋማት ጋር ይበልጥ ትስስር ለመፍጠርና በጋራ ለመስራትና በዘርፉ ስለሚፈጠሩ ክስተቶችና መልካም ተሞክሮዎች ዙሪያ ወቅታዊ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሚችል አመልክተዋል፡፡ 240 የሚሆኑ አባላት ያሉት ይህ ፎረም ከ190 በላይ አገራት የሚሰሩ የዘርፉን ባለሙያዎችን ያስተሳሰረ ሲሆን በተለያዩ የአለም ክፍሎች የሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ ተቋማት የፋይናነስ አገልግሎትና ድጋፍ በሚያገኙባቸው አማራጮች ዙሪያ አተኩሮ ይሰራል፡፡