Select Page

“ይህ ዕድል እኔን ለመሰሉ አነስተኛ ማሳ ላላቸው አርሶ አደሮች በጎ ተግባር ነው” አርሶ አደር ግርማ በዳሶ

አርሶ አደር ግርማ በዳሶ በአርሲ ዞን ሙኔሳ ወረዳ ኗሪ ናቸው፡፡ በግብርና ስራ ላይ ተሰማርተው ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩት አቶ ግርማ ያላቸው አነስተኛ የሚባል ማሳ እና ከኢኮኖሚ ጋር የተያየዙ የአቅም ውስንነቶች በሚፈልጉት ደረጃ የግብርና ሥራቸውን ለማዘመን እንቅፋት ሆኖባቸው ቆይቷል፡፡

አርሶ አደር ግርማ “አሁን አዲስ ጊዜ መጥቷል” ይላሉ፤ የግብርና ስራቸውን የሚያስፋፉበትና ገቢያቸውን የጨመሩበት መልካም የሚባል ጊዜ፡፡

ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ዳሸን ባንክ እና ግብርናን በቴክኖሎጂ በማዘመን ላይ ትኩረት አድርጎ ከሚሰራ “ለእርሻ” የተሰኘ ሐገር በቀል ተቋም እንዲሁም ከሱፍሌት ማልት ኢትዮጵያ ጋር በጋራ በመሆን አቶ ግርማን የመሰሉ አነስተኛ ማሳ ያላቸውን አርሶ አደሮች አቅማቸውን ለማሳደግ በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም ኢንተርናሽናል ፋይናስ ኮርፓሬሽን የተሰኘው ተቋም የቴክኒክ ድጋፍ ያደርጋል፡፡

ዳሸን ባንክ ያለምንም ማስዥያ አርሶ አደሮች ብድር እንዲያገኙ በማመቻቸት፣ለእርሻ የተሰኘው ተቋም ደግሞ አርሶ አደሩ ግብርናውን እንዲያዘምን የሚያግዙ ስልጠናዎችን በመስጠትና የግብርና ግብዓቶች እንዲቀርቡ በማመቻቸት ይሰራሉ፡፡ ሱፍሌት የተሰኘው ኩባንያ ደግሞ አርሶ አደሩ ያመረተውን ገብስ ያለማንም ጣልቃ ገብነት በቀጥታ ግዥ በመፈፀም በጋራ እየሰራ ይገኛል፡፡

የአርሲ ዞን ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ግርማ ሶስቱ ተቋማት በጋራ ሆነው የፈጠሩት ይህ ዕድል አርሶ አደሩ ምርታማ እንዲሆንና የኢኮኖሚ አቅሙ እንዲያድግ ማስቻሉን ይናራሉ፡፡

“በተለይም ይህ ዕድል እኔን ለመሰሉ አነስተኛ ማሳና የግብርና ግብዓት ለማሟላት የአቅም ውሥንነት ላለባቸው አርሶ አደሮች እፎይታ የሰጠና የሚመሰገን በጎ ተግባር ነው” ይላሉ፡፡

ዳሸን ባንክ፣ለእርሻ እና ሱፍሌት በጋራ ሆነው እያከናወኑት በሚገኘው በዚህ ተግባር አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በዳሸን ባንክ የኤም ኤስ ኤም ኢ(MSME) ከፍተኛ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ወንድማገኝ ጌታቸው ዳሸን ባንክ፣ለእርሻ እና ሱፍሌት ማልት ኢትዮጵያ ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን አነስተኛ ማሳ ያላቸውን አርሶ አደሮች ለማገዝ በትብብር እየሰሩ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

በዚህም ዳሸን ባንክ በዘንድሮው ዓመት ለ166 አርሶ አደሮች 3.78 ሚሊየን ብር የሚደርስ ብድር ማቅረቡን ተናግረዋል፡፡ ሶስቱ ተቋማት በደረሱት የሶስትዮሽ ስምምነት መሰረትም አሁን ላይ ፕሮጀክቱ በአርሲ ዞን አራት ወረዳዎች ላይ እየሰራ ይገኛል፡፡

ዳሸን ባንክ የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ እያከናወናቸው ከሚገኙ ተግባራት መካከል በግብርናው ዘርፍ የሚሰራው ስራ አንዱ እንደሆነ የሚያስረዱት አቶ ወንድማገኝ አሁን ላይ በሙከራ ደረጃ እየተከናወነ በሚገኘው ስራ አመርቂ የሚባል ውጤት መታየቱን አብራርተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ብድር ለማግኘት ለሚቸገሩ አርሶ አደሮች በሚፈልጉት ጊዜ በመድረስ የግብርና ግብአቶችን እንዲያሟሉ፣የክህሎት ማሻሻያ ስልጠናና ምክር እንዲያገኙ እንዲሁም ምርታቸውን በተገቢው ዋጋ ሸጠው ውጤታማ እንዲሆኑ እያስቻለ ይገኛል፡፡

ዳሸን ባንክ ይህን መሰል የፋይናንስ አካታችነት ስራዎችን እያሰፋ እና ማሕበራዊ ሐላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት የሚያስችሉ ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ ወንድማገኝ ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ በሙከራ ደረጃ እየተሰራበት የሚገኘው አነስተኛ ማሳ ያላቸውን አርሶ አደሮች የማገዝ ስራ በማጠናከር ወደ ሌሎች የሐገሪቱ አካባቢዎች የማስፋት ዕቅድ እንዳለም ጠቁመዋል፡፡

ለእርሻ የተሠኘው ተቋም ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ አብርሐም እንድሪያስ በበኩላቸው ድርጅታቸው ግብርናውን ለማዘመን የሚያግዝ ዲጂታል አማራጮች በማበልጸግ አርሶ አደሩን እየደገፈ እንደሚገኝ ነግረውናል፡፡

አሁን ላይም አርሶ አደሩ በዋናነት ያለበትን የፋይናንስና ገበያ ችግሮች ለመፍታት ከሌሎች ተቋማት ጋር እየተከናወነ በሚገኝ የትብብር ስራ በጋራ ውጤት ማምጣት እየተቻለ እንደሆነም አቶ አብርሐም አመላክተዋል፡፡

አነስተኛ ማሳ ያላቸውን አርሶ አደሮች በሁሉም መስክ ለማገዝ ከዳሸን ባንክ ጋር በተደረሰ ስምምነት እየተከናወነ በሚገኘው በዚህ ፕሮጀክት የአርሶ አደሩ ምርት በአማካይ ቀድሞ ከነበረበት 24 በመቶ በላይ ማደጉንና ገቢያቸው ደግሞ የ39 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን በጥናት ማረጋገጥ ችለናል ብለዋል፡፡

በዚህ የሙከራ ፕሮጀክት ላይ ሴት እና ወጣት አርሶ አደሮች ጭምር ተጠቃሚ መሆናቸውን የጠቁሙት ማኔጅንግ ዳይሬክተሩ ዳሸን ባንክ ለአርሱ አደሩ ቀለል ያለ የብርድ ስርዓት በማመቻቸት ያከናወነው ተግባር እንደ ሐገር የፋይናንስ አካታችነትን ለማሳየት ጥሩ ሞዴል እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

Facebook
Twitter
YouTube
LinkedIn
Instagram
Telegram