Select Page

ኢትዮ ቴሌኮም ከዳሽን ባንክ ጋር በአጋርነት የቴሌብር የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎቶችን በዛሬው ዕለት አስጀመረ

ቴሌብር የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት ለማህበረሰባችን በተለይም በዋናነት መደበኛ የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ላልሆነው የማህበረሰብ ክፍል ሁለንተናዊ ለውጥና መሻሻል ከፍተኛ ሚና ያላቸውን፣ እንዲሁም የፋይናንስ አገልግሎት ከማግኘት ባሻገር ትርጉም ያለው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ የሞባይል አነስተኛ ብድር፣ የኦቨርድራፍትና የቁጠባ አገልግሎቶችን ከዳሽን ባንክ ጋር በአጋርነት መስጠት እንዲችል እ.ኤ.አ ነሐሴ 01 ቀን 2022 በደብዳቤ ቁጥር FIS/PSSD/218/2022 ከብሔራዊ ባንክ በተሰጠው ፈቃድ መሰረት አገልግሎቱን በዛሬው ዕለት አስጀምሯል፡፡

ዳሽን ባንክ በሀገራችን ካሉ የግል ባንኮች በቀዳሚነት ኢንዱስትሪውን በመቀላቀል ባለፉት 25 ዓመታት የባንክ አገለግሎትን በማዘመን አገራችን የሰለጠነው ዓለም በደረሰበት እርምጃ ልክ እንድትጓዝ ለማድረግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በማስተዋወቅ ቀዳሚ የፋይናንስ ተቋም ነው፡፡ ባንኩ ቅርንጫፎቹንና የሥራ ክፍሎቹን በመረጃ መረብ ከማገናኘት አንስቶ የኤሌክትሮኒክ የክፍያ ሥርዓትን ጨምሮ በሞባይል በኢንተርኔትና በዲጂታል የገንዘብ ዝውውር፣ ወረቀት አልባ የገንዘብ ፍሰትን በማስተዋወቅ የቀዳሚነት ሚናውን እየተወጣ ያለ በግሉ ዘርፍ አንጋፋና ተመራጭ ተቋም ነው፡፡ ዳሸን ባንክ የዓለም አቀፍ የሃዋላ አገለግሎት ሠጪ ተቋማት ጋር አብሮ በመሥራትም ቀዳሚ ነው፡፡ ራዕይና ተልዕኮው ደንበኛ ተኮር በሆነና ሙያን በዕውቀትና ልምድ ባከበረ አሠራር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ አገርንና ህዝብን እያገለገለ ይገኛል፡፡ ለባንክና የፋይናንስ አገልግሎት ሩቅ የሆነውን የኅብረተሰብ ክፍል በምልዓት ለመድረስ እንዲችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በማስፋፋት ቀላልና ምቹ የአገልግሎት አማራጮችን በማቅረብ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ባለው የዓላማና ግብ ተመሳሳይነት የተነሳ ሁለቱ ተቋማት የፋይናንስ አገልግሎትን በትብብር አቅርበዋል፡፡

ቴሌብር መላ የተሰኘውን የአነስተኛ ብድር አገልግሎት በቴሌብር አካውንታቸው አማካኝነት የሚያገኙበት፣    የቴሌብር ደንበኞች በአካውንታቸው ላይ ያላቸው ቀሪ የሂሳብ መጠን በቂ ባልሆነበት ጊዜ የሚጠቀሙት ቴሌብር እንደኪሴ የተሰኘ የክሬዲት ክፍያ/ኦቨርድራፍት ብድር አገልግሎት እንዲሁም ቴሌብር ሳንዱቅ የተሰኘ ደንበኞች ከወለድ ነጻ ወይም የተለያየ የወለድ መጠን የሚታሰብባቸው የቁጠባ አይነቶችን የሚጠቀሙበት የቴሌብር ፋይናንስ አገልግሎት ለደንበኞቹ በቴሌብር መተግበሪያ እና በአጭር ቁጥር (*127#) አቅርቧል፡፡

የቴሌብር የአነስተኛ ብድር አገልግሎትን ልዩ የሚያደርገው በገጠርም ሆነ በከተማ ያሉ ደንበኞች ተያዥ ሳያስፈልጋቸው ያለዋስትና (without collateral) የቴሌብር እና የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቶች ተጠቃሚ በመሆናቸውና ባከናወኗቸው የቴሌብር ግብይቶች መሰረት በአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ሲስተም አማካኝነት የክሬዲት ስኮሪንግ ተሰልቶ የብድር አገልግሎት ማግኘት መቻላቸው ሲሆን የተበደሩትን ብድር በወቅቱ በመመለስና ሰፋ ያሉ ግብይቶች በመፈጸም የክሬዲት ስኮር ነጥባቸውን ወይም መበደር የሚችሉት የገንዘብ መጠን ማሳደግ ይችላሉ፡፡

በዚህ አገልግሎት ኩባንያችን በመጀመሪያው ዓመት ውስጥ በአጠቃላይ በሶስቱም አገልግሎቶች (በአነስተኛ ብድር፣ በኦቨርድራፍት እና በቁጠባ) ከ12.8 ሚሊዮን ደንበኞችን ተጠቃሚ በማድረግ በአጠቃላይ ከ108 ሚሊዮን በላይ የግብይት ቁጥርና ከ19.5 ቢሊዮን ብር በላይ መጠን ያለው የብድርና የቁጠባ ግብይት ለማከናወን አቅዶ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡

ይህም በሀገራችን ከፋይናንስ አካታችነት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ማነቆዎችን ለመፍታት፣ የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎት ዘመናዊ አሠራርንና የፋይናንስ መሠረተ ልማት አገልግሎትን ለማጠናከር፣ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ ያልሆኑትን የህብረተሰብ ክፍሎች ያለ መደበኛ የባንክ ሂሳብ አሠራር በሞባይል ስልካቸው ብድር እና ቁጠባ የመሳሰሉ አገልግሎቶችን በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ በተለይም የባንክ አገልግሎት ማግኘት የማይችለውን ማህበረሰብ ወደ መደበኛው የፋይናንስ አገልግሎት በማምጣቱ እና በማካተቱ ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወት ይሆናል፡፡

ለሀገራችን ፈር-ቀዳጅና ሰፊውን የማህበረሰባችን ክፍል ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችለውን የቴሌብር የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት በዛሬው ዕለት በማስጀመር የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ እውን የማድረጉን ተግባር አጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ በቀጣይም በህብረተሰባችን የአኗኗር ዘይቤ ላይ ለውጥ የሚያመጡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እና አሰራሮችን ተግባራዊ የሚያደርግ ይሆናል፡፡

Facebook
Twitter
YouTube
LinkedIn
Instagram
Telegram