Select Page

ዳሸን ባንክና የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ

(ጋምቤላ፣ ነሐሴ 27 ቀን 2014 ዓ.ም) ዳሸን ባንክና የጋምቤላ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በጋምቤላ ክልል የቢዝነስ ስራዎችን ለማስፋት እና ማህበረሰብ ተኮር ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

ዳሸን ባንክ በክልሉ ለሚገኙ አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ብድር እንዲዉል ለክልሉ ማይክሮፋይናስ ተቋም 25 ሚሊየን ብር በአነስተኛ ወለድ በክልሉ መንግስት ዋስትና የሚያቀርብ ይሆናል፡፡

ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት ዳሸን ባንክ በክልሉና ከክልሉ ውጭ የዩኒቨርስቲ ትምህርት በመከታተል ላይ ለሚገኙና በቂ ገቢ ለሌላቸው 100 የክልሉ ወጣቶች የትምህርትና ሌሎች ግብአቶች ክፍያ የሚውል 1 ሚሊየን ብር ለክልሉ መንግስት ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብቷል፡፡
ስምምነቱ ክልሉ በግብርና፣ በቤቶች ልማትና ሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አገልግሎቶች ዙሪያ ዕድገት ለማምጣት የሚያደርገውን ጥረት የተለያዩ የባንክ አገልግሎቶችን በማቅረብ ለማገዝ እንደሚያስችልም ተነግሯል፡፡

የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ፒተር ሃውቦል የክልሉ መንግስት ባንኩ ድጋፍ የሚያደርግላቸውን ተማሪዎች ስም ዝርዝርና ሌሎች ተያያዥ መረጃዎች አዘጋጅቶ ያቀርባል ብለዋል፡፡ ክልሉ ዳሸን ባንክ የራሱን ህንፃ ለመገናባትና ተጨማሪ ቅርንጫፎችን ለመክፈት የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝ ዝግጁ መሆንም አመልክተዋል፡፡

በስምምነት ስነስርአቱ ላይ የባንኩ ቺፍ – ስትራቴጅና ኢኖቬሽን ኦፊሰር አቶ ሙሉጌታ አለባቸው ክልሉ ያለውን አቅም በመጠቀም ወደተሻለ የእድድት ደረጃ ለመድረስ ያሚያደርገውን ጥረት በሙሉ አቅሙ እንደሚደግፍ ገልጸዋል፡፡

ዳሸን ባንክ በጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ስምንት ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን በነዚህ ቅርንጫፎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ቋሚና ጊዜያዊ ሰራተኞችን በማሰማራት ለደንበኞቹ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

Facebook
Twitter
YouTube
LinkedIn
Instagram
Telegram