ዳሸን ባንክ ለኢትዮጵያ ባንኮች የመጀመሪያ የሆነውን የ40 ሚሊየን ዶላር ብድር አገኘ
– ባንኩ ያገኘው ብድር ለወጪ ንግድ የሚሰጠውን ብድር ይበልጥ እንዲያጠናክር ያስችለዋል፡፡
– ለውጭ ምንዛሪ የሚሰጠው ብድር የግብርና ምርት ላኪዎች አዳዲስ ማሽነሪዎችን በመግዛት የምርት ሂደታቸውን እንዲያዘምኑና ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ያግዛል።
– የኢትዮጵያ የግብርና ምርት ላኪዎችን የገቢ አቅም በማሳደግ ምርታማነትን ያሳድጋል፡፡
(አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23 ቀን 2023)- የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት (ቢ አይ አይ) እና የኔዘርላንድ የስራ ፈጠራና ልማት ባንክ የሆነው ኤፍ ኤም ኦ እያንዳንዳቸው 20 ሚሊየን ዶላር በድምሩ 40 ሚሊየን ዶላር ብድር በኢትዮጵያ ቀዳሚ ከሆኑት ባንኮች አንዱ ለሆነው ለዳሸን ባንክ ማቅረባቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ ይህ የብድር አቅርቦት ኢትዮጵያ ለውጪ ገበያ የምታቀርበውን የግብርና ምርት ለማሳደግ እና በእጅጉ አስፈላጊ የሆነውን የውጪ ምንዛሬ አቅርቦት ለማሻሻል ያስችላል፡፡
ቢ አይ አይ እና ኤፍኤምኦ ለዳሸን ባንክ ያቀረቡት ገንዘብ በኢትዮጵያ 80% የህብረተሰብ ክፍል በተሰማራበት፣ ለጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት 39 % ድርሻ ላለው እና ለወጪ ንግዱ 90 % አስተዋጽኦ ለሚያበረክተው የግብርና ዘርፍ ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡
የቀረበው ብድር ባንኩ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ ለሚያደርገው ጥረት የበኩሉን እገዛ ያደርጋል፡፡ በተለይ በእርሻ ስራ ላይ ለተሰማሩ ምርታማነትን ለመጨመር የሚያስችሉ ግብአቶችን በማሟላት ከኤክስፖርት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡
ብድሩ በሀገሪቱ ከፍተኛ እጥረት በሚታይበት የውጭ ምንዛሪ በመቅረቡ ባንኩ ዓይነተ-ብዙ አገልግሎቶችን ለደንበኞቹ ለማቅረብ የሚያግዝ ይሆናል፡፡ ይህም በአመራረት፣ በማጓጓዝ እና በማቀናበር ሂደቶች ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ዘመናዊ መሳሪያዎችን ከውጭ ለማስገባት የውጭ ምንዛሪ ማቅረብን ይጨምራል፡፡
የፋይናንስ ተቋማት ትብብር ለግሉ ዘርፍ እድገት ጉልህ ሚና አለው፡፡በዚህ ትብብር ቢአይአይ እና ኤፍኤምኦ. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እ.ኤ.አ በ 2021 አዲስ ባወጣው የውጭ ማንዛሪ ማቀላጠፊያ መመሪያ መሠረት በኢትዮጵያ ለሚገኝ የፋይናንስ ተቋም በውጭ ምንዛሪ የቀረበ የረዥም ጊዜ ብድር ሲሰጡ የመጀመሪያዎቹ ናቸው፡፡ይህ ፋና ወጊ ተግባር ገበያውን በማነቃቃት ከዓለም አቀፍ መዋዕለ-ንዋይ አቅራቢዎች ተጨማሪ ሀብት ለማሰባሰብ መተማመንን ለመገንባት ያግዛል፡፡
በሚቀጥሉት አስር አመታት በአማካይ በ6.2 በመቶ እንዲያድግ ከሚጠበቀው የኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ አንጻር በቢአይአይ እና ኤፍኤምኦ የቀረበው ፋይናንስ ኢትዮጵያውያን ላኪዎች ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ እንዲያመነጩ ከእነሱ አልፎም ለላኪዎቹ ምርታቸውን የሚያቀርቡ አነስተኛ አምራቾች ምርታቸውን በቀጣይነት በማሳደግ ከውጭ ንግዱ ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው፡፡
በግብርና ለተሰማሩ የንግድ ተቋማት የሚቀርብ ፋይናንስ ከአበባ እስከ ቡና እና የቁም ከብት ድረስ የተሻሻሉ የአመራረት ዘዴዎችን ለማስተዋወቅ፣ ጥራትን ለማሳደግ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ለማሟላት እና እሴት ለመጨመር የጎላ ሚና ይኖረዋል፡፡ የፋይናንስ አቅርቦቱ በግብርና ወጪ ንግድ ዙሪያ የተሰማሩ አምራቾችና ነጋዴዎችን የኢኮኖሚ አቅም በማጎልበት ከ 45 በመቶ ያልበለጠ የማህበረሰብ ክፍል ብቻ የባንክ አካውንት ባለቤት በሆነባት ሀገራችን የፋይናንስ አካታችነትን ለማሳደግ አጋዥ ይሆናል፡፡
በዚህ ትብብር ቢአይአይ እና ኤፍኤምኦ ከዳሸን ባንክ ጋር በአመራር ስጋት አስተዳደር፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በማህበራዊ እና ስርዓተ – ጾታ ዘርፎች ዙሪያ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን በኢትዮጵያ ለማስተዋወቅ እና ለማስረፅ በቅርበት ይሰራሉ፡፡
የዳሸን ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ዓለሙ እንደገለጹት ” ተምሳሌታዊ በሆነው ቢአይአይ እና ኤፍኤምኦ በትብብር የሰጡን ብድር የውጭ ምንዛሪ ማመንጨት የሚችሉ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ከውጭ የፋይናንስ ተቋማት በኢትዮጵያውያን ባንኮች በኩል ፋይናንስ ማግኘት የሚችሉበትን የብሄራዊ ባንክ መመሪያ ተግባራዊ በማድረግ ፋና ወጊ በመሆናችን ደስታችን የላቀ ነው፡፡ በውጭ ምንዛሪ የቀረበው ብድር በውጭ ንግድ ላይ የተሰማሩ ደንበኞችን ለማገዝ እንደሚውል እና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በእጅጉ የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ባንካችን ከሁለቱ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በመስራቱ ለሀገር የሚተርፍ በርካታ ልምድ፣ እውቀትና የአሰራር ዘይቤ ተቀስሟል፡፡ ባንካችን ከሁለቱ የልማት አጋሮቹ ላገኘው ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና አለን ” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም ሁለቱ ተቋማት በዳሸን ባንክ ውጤታማነትና በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ላይ ሙሉ እምነት በመጣል የፋይናንስ አቅርቦት በማድረጋቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸውም ዋና ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡
የቢ አይ አይ ዋና ስራ አስፈጻሚና የፋይናንሺያል አገልግሎት ኃላፊ የሆኑት ስቴፈን ፕሪስትሊ በአለምአቀፍ ኢንቨስትመንት ላይ የመጀመሪያዎቹ ተቋማት በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ቢ አይ አይ በኢትዮጵያ ከ50 አመታት በፊት ኢንቨስት ማድረጉንም አስታውቀዋል፡፡ ” በዚህ የፋይናንስ አቅርቦት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እየከፈተ ወዳለው ገበያ ቀድመን ለመግባት ከቀዳሚዎቹ ውስጥ በመሆናችን ኩራት ተሰምቶናል፡፡ባለፉት 50 ዓመታት ቢአይአይ በኢትዮጵያ ቀዳሚ መዋዕለ-ነዋይ አፍሳሽ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከኤፍኤምኦ ጋር የደረስንበት አጋርነት ወደ ኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ በልማት የፋይናንስ አቅራቢዎችና የንግድ መዋዕለ-ንዋይ አንቀሳቃሾች ትብብር ሊመጣ የሚችለውን ከፍ ያለ ሀብት አመላካች ነው፡፡ ” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የኤፍ ኤም ኦ የፋይናንሺያል ኢንስቲትዩሽን ዲፓርትመንት ዳይሬክተር ማርኒክስ ሞንስፎርት እንደተናገሩት” ዳሸን ባንክ እና ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ መዋዕለ-ንዋይ እና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እንዲያገኙ በሚያስችለው በዚህ ፈር ቀዳጅ አጋጣሚ በመሳተፋችን ደስተኞች ነን፡፡ በእጅጉ አስፈላጊ የሆነውን በውጭ ምንዛሪ ብድር በውጪ ንግድ ላይ ያተኮረ ግብርና በመደገፍ ለሥራ ፈጠራና በገጠር አካባቢ የፋይናንስ አካታችነትን በማስፈን አስተዋጽኦ ለማድረግ ህልማችን ነው፡፡ ለዚህ ታላቅ ትብብር ዳሸን ባንክን እና ቢአይአይን እናመሰግናለን፡፡ ” በማለት ገልጸዋል፡፡