Select Page

ዳሸን ባንክ ከብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በትብብር ለመስራት ስምምነት ፈጸመ

(ሚያዚያ 28 ቀን 2014 ዓ.ም/ አዲስ አበባ) ዳሸን ባንክ እና ናሽናል አይዲ ፕሮግራም የዳሽን ባንክ ደንበኞችን የዲጂታል አይዲ እንዲያገኙ የሚያስችል እና ባንኩ በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚደራጅ የማንነት ምዝገባ መረጃ ስርአት ተጠቃሚ የሚያደር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

በሃገሪቱ ዜጎች የሚለዩበት ዘመናዊ ብሄራዊ መታወቂያ አለመኖሩ የባንክ ዘርፉን እድገትና የዚጎችን የፋይናንስ ተጠቃሚነት በእጅጉ ገድቦት እንደቆየ የሚታወቅ ሲሆን ይህንኑ ችግር ለመቅረፍ ብሄራዊ የመታወቂያ ፕሮግራም ይፋ ሆኖ እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቷል። ፕሮግራሙ ዜጎች የተለይ ብሄራዊ መታወቂያ እንዲኖራቸው በመስራት ላይ ነው። ለፕሮግራሙም ስኬት በተለያዩ መስኮች ከሚሰሩ አጋር አካላት ጋር የትብብር መዕቀፍ በመፍጠር ላይ ይገኛል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ባወጣው መመሪያ መሰረት ሁሉም የገንዘብ ተቋማት የደምበኞቻቸውን ዝርዝር መረጃ በሚገባ በማጣራትና በማደራጀት በመረጃ ቋት መዝግበው መያዝ እንዳለባቸው መደንገጉ የሚታወስ ነው።

ይህንን መመሪያ ከማስፈጸም ብሎም የብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራምን ከግብ ለማድረስ ባንኩ ቁርጠኝነቱን በማሳየት ከፕሮግራሙ ማስተባበሪያ ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ፈጽሟል። በስምምነቱ መሰረት የፕሮግራሙን ግቦች በማሳካት የፋይናንስ አካታችነትን ለማሳደግና ሃብትን በማቀናጀት ለመስራት ከስምምነት ላይ ተደርሷል። ፕሮግራሙ የዜጎችን ልዩ የሆነ መለያዎችን ማለትም የጣት አሻራ፤ የአይን አሻራ እና የፊት መልክን በኤሌክትሮኒክ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ለመለየት የሚያስችል አሰራር ነው፡፡

በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ወቅት እንደተገለጸው ልዩ የዲጂታል መታወቂያ (Unique Digital ID) በባንኩ መተግበሩ ሀገራዊ ፋይዳው ከፍተኛ እንደሆነና ወደፊትም ልዩ የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ የሚሆኑ ደንበኞች በየትኛውም ቦታ ሆነው የገንዘብ ተቋማትን ለመጠቀም ቢፈልጉ ማንነታቸው በቀላሉ ስለሚለይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን እንደሚቀርፍ ተገልጿል፡፡

Facebook
Twitter
YouTube
LinkedIn
Instagram
Telegram