ዳሸን ባንክ የፀሐይ ኃይልን መጠቀም የሚያስችሉ የሶላር ፓኔል ገጠማ አስጀመረ
ዳሸን ባንክ የፀሐይ ኃይልን መጠቀም የሚያስችሉ ሶላር ፓኔል በዋናው መስሪያ ቤትና ቅርንጫፎች ጣሪያ ላይ እያስገጠመ ይገኛል።
ዳሸን ባንክ የአካባቢ፣ ማኀበራዊ እና አስተዳደር (ESG) መርሆችን ከአገልግሎቱ ጋር በማዋሃድ ማኀበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት ተግባራት ላይ ግንባር ቀደም ሆኖ እየሰራ ይገኛል።
ባንኩ አሁን ላይ እያከናወነ ያለው ተግባር የዚህ አካል መሆኑን የተናገሩት በዳሸን ባንክ የኢኤስጅ ስፔሻሊስት አቶ ፍስሐ አዱኛ ታዳሽ ኃይልን በመጠቀም ለአየር ንብረት ለውጥ የድርሻችንን ለመወጣት ጥረት እያደረግን ስለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።
ስራው ባንኩ ለኃይል አቅርቦትነት የሚጠቀማቸውን ጀኔረተሮች በፀሐይ ኃይል ለመተካት እንደሚያስችልም አብራርተዋል። ከዚህ ባሻገር ባንኩ ከሚሰጣቸው ዘመናዊ አገልግሎቶች በተጨማሪነት በመሰል ተግባራት የአካባቢ ብክለትን በመቀነስ ማህበረሰቡ ላይ ሊደርሱ የሚችልን የጤና እክሎች ለመከላከል ያስችላል ብለዋል።
የበካይ ጋዝ ልቀትን በመቀነስ ረገድ ከፍ ያለ አስተዋፅኦ እንዳለው ያነሱት አቶ ፍስሐ ባንኩ በዚህ ተግባሩ የማህበረሰብ ጤና አጠባበቅ ላይ አሻራውን ለማሳረፍ እንደሚያግዘው አመላክተዋል።
ዳሸን ባንክ ለአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ፈር ቀዳጅ ተግባራትን ማከናወኑን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
በዳሸን ባንክ ኢንጅነሪንግ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ታዲዎስ ላዕከማርያም በበኩላቸው ዳሸን ባንክ የሶላር ፓኔል ተከላ ስራዎችን በሁሉም ቅርንጫፎች ለማከናወን አቅዶ ወደ ተግባር መግባቱን ገልጸዋል።
አሁን ላይ በዳሸን ባንክ ዋናው መስሪያ ቤት እየተገጠሙ ያሉ ሶላር ፓኔሎች 54 ያህል እንደሚሆኑ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ እነኝህ ፓኔሎች 29 ኪሎዋት የሚደርስ የፀሐይ ሃይል ለማመንጨት የሚያስችሉ ናቸው። በተመሳሳይ በሌሎች የባንኩ ቅርንጫፎች የሚገጠሙ ሶላር ፓኔሎች የፀሐይ ኃይልን በስፋት ለማግኘት የሚያስችሉ እንደሆኑም አስረድተዋል።
ዳሸን ባንክ ለዘላቂ ልማት ያለውን ቁርጠኝነት በሚያንፀባርቁ የአካባቢ፣ ማህበራዊ እና አስተዳደራዊ ተግባራት ላይ በስፋት በመሳተፍ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ መሰል ስራዎች ለአካባቢ ጥበቃ አስተዋጽኦ ከማድረግ ባለፈ የስራ እድል በመፍጠር እና የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማጎልበት ማህበራዊ አጋርነትን የሚያበረታቱ ናቸው፡፡