Select Page

አዲሱ የዳሸን ባንክ ቦርድ አቶ ዱላ መኮንንን በድጋሚ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀ-መንበር አድርጎ መረጠ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 08 ቀን 2016 ዓ.ም- የዳሸን ባንክ ባለአክሲዮኖች ባካሄዱት 30ኛው መደበኛ ጉባኤ የተመረጠውና የምርጫውም ውጤት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፀደቀለት አዲሱ የዳሸን ባንክ ቦርድ ባደረገው የመጀመሪያ ጉባኤ ላይ ባለፉት ሶስት ዓመታት ባንኩን በዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀ-መንበርነት ያገለገሉትን አቶ ዱላ መኮንንን በድጋሚ በዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀ-መንበርነት መርጧል፡፡

አዲሱ ቦርድ የካቲት 05፡ 2016 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል ባካሄደው ጉባኤ ለቀጣይ ሶስት አመታት ዳሸን ባንክን በዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀ-መንበርነት እንዲያገለግሉ በድጋሜ የመረጣቸው አቶ ዱላ መኮንን በአሁኑ ወቅት የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የማዕድን ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡

አዲሱ ሊቀመንበር አቶ ዱላ መኮንን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ፣ እንዲሁም የማስተርስ ዲግሪያቸውንም በቢዝነስ አስተዳደር ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ በአግሪካልቸራል ምህንድስናም ዲፕሎማ አላቸው፡፡

አቶ ዱላ በወንጂ ሸዋ፣ መተሃራ እና ፊንጫ ስኳር ፋብሪካዎች እንዲሁም በሌሎች ተቋማት በአጠቃላይ ለ24 አመታት አገልግለዋል፡፡ በሊሙ ቡና ልማት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የሰሩት አቶ ዱላ ከዚያ በኋላም የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅም ነበሩ፡፡ የኢትዮ ሌዘር ኢንዱስትሪ ኃ/የተወ/የግል/ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ዱላ በሆራይዘን ፕላንቴሽን ኃ/የተወ/የግል/ኩባንያም በከፍተኛ ኃላፊነት ሰርተዋል፡፡

አዲስ የተመረጡት የቦርድ አባላት እና ባንኩን ላለፉት ሶስት ዓመታት ያገለገሉት የቦርድ አባላት የስራ ርክክብ ያደረጉ ሲሆን ንዑስ ኮሚቴዎችንም አዋቅረዋል፡፡ ባንኩ አዲስ ለተመረጡት የቦርድ አባላት አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴውን አስመልክቶ ገለፃ ሰጥቷል፡፡

Facebook
Twitter
YouTube
LinkedIn
Instagram
Telegram