Select Page

ዳሸን ባንክና ማስተርካርድ የመጀመሪያውን ቨርቹዋል አለም አቀፍ ቅድመ ክፍያ ካርድ አስተዋወቁ

አዲስ አበባነሃሴ 09-2015 . ዳሸን ባንክ አለም አቀፍ ቅድመ ክፍያ ካርድ ከማስተርካድ ጋር በመተባበር ከተለመደው በስም ከሚታተም የፕላስቲክ ካርድ በተጨማሪ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነ ቨርቹዋል ካርድን በማምጣት  ዛሬ በሸራተን አዲስ ሆቴል አስተዋውቀዋል፡፡

የዳሸን ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ዓለሙ በስነ-ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ዳሸን ባንክ ይህን በአይነቱ የተለየ ካርድ ማስተዋወቁ ባንኩ ለደንበኞቹ ቀላል፣ ምቹና አስተማማኝ የፍይናንስ አገልግሎቶችን ይበልጥ ለማቅረብ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል፡፡

ካርዱ ደንበኞች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ገንዘባቸውን ያለምንም ስጋት መጠቀም የሚችሉበት አማራጭ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የማስተርካርድ የምስራቅ አፍሪካ ስራ አስኪያጅ ሸህርያር አሊ በበኩላቸው ማስተርካርድ ከዳሸን ባንክ ጋር የፈጠረው ጥምረት በኢትዮጵያ እንደ አለም አቀም ካርድ ያሉ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ ማህበረሰቡ ይበልጥ የዲጂታል አገልገሎቶችን ተጠቃሚ እንዲሆን ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚፈጥር ገልፀዋል፡፡

“ከዳሸን ባንክ ጋር በመጣመር የተለያዩ የዲጂታል አገልግሎቶችን ለማቅረብና ይህን መሰል የክፍያ አማራጭ ለንግዱ ማህበረሰቡና ሌሎች ደንበኞች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻላችን ትልቅ ክብር ይሰማናል” ብለዋል፡፡

በዳሸን ቅድመ ክፍያ ማስተርካርድ ደንበኞች ከኤቲኤም እና ፖስ በተጨማሪ በኢ-ኮሜርስ ክፍያ መክፈል የሚያስችላቸው ሲሆን ደንበኞች ፕላስቲክ ወይም ቨርቹዋል ካርድ በመውሰድ መጠቀም ይችላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ፕላስቲክ ካርዱ ስም የታተመበትና ስም ያልታተመበት የካርድ አይነቶችን የያዘ ነው፡፡

ደንበኞች ዳሸን ማስተር ካርድ ላይ የተሞላው የውጪ ምንዛሬ ሲያልቅ እንደገና በመሙላት መጠቀም የሚያስችላቸው ሲሆን ካርዱን ኤቲኤምና ፖስ ማሽን ላይ በማስገባት ወይም ያለ ንክኪ ገንዘብ ማውጣት ወይም ክፍያ መፈፀም  ያስችላቸዋል፡፡

ፕላስቲክ ካርዱ በሚስጢር ቁጥር የተጠበቀ ሲሆን ቨርቹዋል ካርዱ ደግሞ በአንድ ጊዜ የይለፍ ቃል ደህንነቱ የተጠበቀ ነው፡፡ ደንበኞች ካርዱን ለመጠቀም አቅራቢያቸው በሚገኝ የዳሸን ባንክ ቅርንጫፍ  ፓስፖርት፣ ቪዛ እና የበረራ ቲኬት በመያዝ አገልግሎቱን ማግኘት ይችላሉ፡፡

ዳሸን ባንክና ማስተርካርድ ከካርዱ በተጨማሪ የንግድ ተቋማት ክፍያቸውን በበይነ መረብ ከየትኛውም የአለም ክፍል መቀበል የሚያስችል የማስተርካርድ የክፍያ መቀበያ ማስተርካርድ ጌትዌይ/ MasterCard Payment Gateway System/ አስተዋውቀዋል፡፡

ይህ የማስተርካርድ ጌትዌይ/ MasterCard Payment Gateway System/ ሦስት የካርድ አይነቶችን በመቀበል የተሻለ የአገልግሎት አማራጭ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ይህም ለንግድ ተቋማት ክፍያ ለመቀበል እና ሽያጭ ለማከናወን  ለምግባረ ሰናይ ድርጅቶች እርዳታ እና የአባልነት ክፍያ ለመሰብሰብ እና ለሌሎች አገልግሎቶች ዘመናዊ የክፍያ መፈጸሚያ መስመር ነው፡፡

 

 

Facebook
Twitter
YouTube
LinkedIn
Instagram
Telegram