Select Page

ዳሸን ባንክ በህንፃዎች ላይ ተከራይተው ለሚገኙ ተከራዮቹ የ 50% ቅናሽ አደረገ

(አዲስ አበባ፣ ግንቦት 03 ቀን 2012 ዓ.ም)  ዳሸን ባንክ አ.ማ. በአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ አርባ ምንጭ፣ ሐዋሳ፣ ባህርዳር፣ ደብረብርሃን፣ ደሴ፣ ዲላ፣ ድሬዳዋ፣ ጎንደር፣ ኮምቦልቻ፣ ወልዲያ፣ ወላይታ፣ ቦንጋ እና ጅማ ከተሞች ላይ በሚገኙ 19 ህንጻዎች ላይ ተከራይተው ለሚገኙ ተከራዮቹ የ50% ቅናሽ አደረገ፡፡

በመላው ዓለም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መስፋፋቱን ተከትሎ የአገራችን ኢኮኖሚ ላይ ቀላል የማይባል ተጽእኖ እያሳደረ እንደሚገኝና በንግድ ዘርፉም ላይ ከፍተኛ መቀዛቀዝ እየታየበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም በንግዱ ኅብረተሰብ ላይ ሊደርስ የሚችለውን የኢኮኖሚ ጫና ለመቀነስ እንዲያስችል ባንካችን ጫናውን እኩል በመጋራት ለህንጻ ተከራይ ደንበኞቹ የ 50% ቅናሽ ኪራይ ዋጋ በማድረግ በ3 ወራት ውስጥ ከተከራዮቹ ያገኝ የነበረውን ብር 3,695,293.16 (ብር ሦስት ሚሊየን ስድስት መቶ ዘጠና አምስት ሺኅ ሁለት መቶ ዘጠና ሶስት ከ16/100) ተቀናሽ አድርጓል ፡፡  በተመሳሳይ መልኩ ከዚህ ቀደም ባንካችን ለኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ መከላከል ዝግጅት የሚውል ገንዘብ እና ሌሎች አቅርቦቶችን ለማሰባሰብ የቀረበውን አገራዊ ጥሪ ተከትሎ፤ በመንግሥት ለተቋቋመዉ ብሔራዊ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ የብር 10,000,000.00 (አስር ሚሊዮን ብር) ድጋፍ ማድረጉ የሚታወስ ነው ፡፡

በቅርቡም  “የኅብረተሰብ ጤና የአገር ደኅንነትና ዕድገት መሠረት ነው” በሚል መሪ ቃል ባንኩ የወስዳቸውን የማኅበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት ግዴታዎች ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን ይህም  ደንበኞችን ከአካላዊ ንክኪ ርቀዉ የባንክ አገልግሎት እንዲያገኙ ከሚያስችሉ ዕርምጃዎች መካከል ኤ.ቲ.ኤም. ማሽኖችን ተጠቅመው ክፍያ በሚፈጽሙ ደንበኞች ላይ ይተገበር የነበረውን የኮሚሽን ክፍያ ሙሉ በሙሉ በማንሳት በነፃ ክፍያ እንዲያከናወኑ፣ ምርቶችን ከውጭ የሚያስገቡ ደንበኞች የሚያጋጥማቸውን የንግድ እንቅስቃሴ መስተጓጎል ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ ከዚህ በፊት ለባንክ መተማመኛ ሰነድ ብድር ወይም ለኤል.ሲ. ማራዘሚያ ይከፍሉ የነበረው ኮሚሽን ተነስቶ ነፃ እንዲሆን፣ በቀጥታ የግዢ ትዕዛዝ ሰነድ ከውጭ ምርት ለሚያስገቡ ደንበኞች ለጊዜ ማራዘሚያ ይከፈሉ የነበረው ኮሚሽን በ50 በመቶ እንዲቀንስ፣ የተበዳሪ ደንበኞች የንግድ እንቅስቃሴ ወረርሽኙ በሚፈጥረው ተፅዕኖ ምክንያት እንደሚቀዛቀዝ በመገመት፤ የተመላሽ ብድሮች የመክፈያ ጊዜ እንዲራዘምላቸው ደንበኞች ጥያቄ በሚያቀርቡበት ወቅት ይከፍሉ የነበረው ኮሚሽን ተነስቶ በነፃ እንዲስተናገዱ፣ ደንበኞች ወደ ባንኩ ቅርንጫፍ ሳይሔዱ የቪዛና የወለድ አልባ አገልግሎት የክፍያ ካርዶቻቸዉን በኤ.ቲ.ኤም. ማሽኖች ሲጠቀሙ  በየቀኑ የሚያወጡት ገንዘብ ላይ እጥረት እንዳያጋጥማቸዉ የዕለት ብር ወጪ መጠን ገደቡ ላይ ማሻሻያ በማድረግ ወደ አሥር ሺሕ ብር ከፍ እንዲል ሲያደርግ፤ ባንኩ ወደ ፊትም  የወቅቱን ሁኔታ እያገናዘበ ተመሳሳይ እርምጃዎችን እንደሚወስድ ማስታወቁ የሚታወስ ነው ፡፡

በዚሁም መሠረት ከላይ ከተጠቀሱት ከፍተኛ ዉሳኔዎች በተጨማሪ ዳሸን ባንክ ወረርሽኙ በህዝባችን ላይ የሚያሳድረውን የጤናና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖዎች በመገምግም፤ ደንበኞቹንና ዜጎቻችንን የሚደግፍ ተመሳሳይ እርምጃዎችን መውሰዱን ይቀጥላል ፡፡

ዳሸን ባንክ ሁልጊዜም አንድ እርምጃ ቀዳሚ !

Facebook
Twitter
YouTube
LinkedIn
Instagram
Telegram